መቀሌ 70 ዕንድርታ እና ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ውድድሮች እንዲወክሉ ተወሰነ
ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች በ2011 ውጤት ይሁን ወይስ ባልተጠናቀቀው የ2012 ውጤት በሚለው ላይ ውይይት ተደርጎ ነበር
መቀሌ 70 ዕንድርታ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፋሲል ከነማ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እንዲሳተፉ ተወስኗል
መቀሌ 70 ዕንድርታ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፋሲል ከነማ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እንዲሳተፉ ተወስኗል
የ 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው መቀሌ 70 ዕንደርታ እና ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው እና የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊው ፋሲል ከነማ በአፍሪካ የውድድር መድረክ ተሳታፊ እንዲሆኑ በሊጉ ካምፓኒ ጠቅላላ ጉባዔ ተወሰነ፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች በ2011 ውጤት ይሁን ወይስ ባልተጠናቀቀው የ2012 ውጤት በሚለው ላይ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ በውይይቱም በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች በ2011 ውጤት መሰረት ይሁን የሚለው በድምጽ ብልጫ አሸንፏል፡፡በዚህም መሰረት መቀሌ 70 ዕንድርታ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፋሲል ከነማ ደግሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን እንዲሳተፉ ነው ውሳኔ የተላለፈው፡፡
የመወያያ ርዕስ ሆኖ የቆየው የተጨዋቾች የ50 ሺ ብር የደመወዝ ገደብ በ2013 ዓ.ም ባለበት እንዲቀጥል እና ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም እንደ አቅሙ እንዲከፍልም ተወስኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በስያሜያቸው ጥያቄ የተነሳባቸው ክለቦች በራሳቸው ፍቃድ ስያሜያቸውን እንዲቀይሩ መወሰኑንም ተሰምቷል፡፡
እየተደረገ ባለው ስብሰባ የኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግ ካምፓኒ በ2013 ዓ.ም ከሊጉ ስያሜ ስምንት ሚሊየን ብር እንደሚጠብቅ አስታውቋል፡፡ ካምፓኒው ከክለቦች ክፍያ ከቴሌቪዥን መብትና ከሊጉ ስያሜ ጋር በአጠቃላይ 29 ሚሊየን ብር ለማግኘት እንዳቀደ አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የፌዴራል ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር ዱቤ ጅሎ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጅማሮ ዙሪያ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ውድድሮች ለጊዜው በዝግ እንዲካሄዱ ፤ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወረርሽኙ ከቀነሰ የተወሰነ ተመልካች እንዲገባ እንደሚደረግና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ይህንን እንደሚያመለክት ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የሚካፈሉ ስፖርተኞችን ጨምሮ ሆቴል ሳይገቡ መጀመሪያውኑ ምርመራ እንደሚያደርጉ የጤናና የጸጥታ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በሀገር አቀፍና በክልሎች ስራው እንደሚመራም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ይህንን መመዘኛ የማያሟላ እንደሚሰረዝና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንደሚከታተለው አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተመሠረቱ ጥቂት ቆይተው የሚፈርሱ ክለቦች እንዳሉ ያነሱት አቶ ዱቤ እነሱን የማጥራትና ደረጃ የመስጠት ሂደት እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ስታዲየምን በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚታደስ ተናግረዋል፡፡
የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያዎች በአግባቡ በመተግበር የቱሪዝም እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።