ኢትዮጵያውያኑ ከመጽሄቱ የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር እንዲካተቱ ማን መረጣቸው?
ኢትዮጵያውያኑ ስለ ስራዎቻቸው መመስከር በቻሉ ሶስት የተለያዩ ሰዎች ነው ከዝርዝሩ ለመስፈር የቻሉት
ታይም መጽሄት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን፣አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ)ን እና ሰአሊ ጁሊ ምሕረቱን ከዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ናቸው ሲል መርጧል
ታይም መጽሄት ኢትዮጵያውያኑን ከዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ናቸው ሲል መርጧል
የዘንድሮው የ“ብሪጅ ሜከር አዋርድ” አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከታይም መጽሔት የ2020 የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ 100 ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ የ2020 “ብሪጅ ሜከር አዋርድ” ሽልማታቸውን በትላንትናው እለት የተቀበሉ ሲሆን ሽልማቱ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆነው እያገለገሉ ላሉ የጤና ባለሙያዎች መታሰቢያ ይሁንልኝ ሲሉ የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታይም መጽሔት የ2020 አንድ መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ከተካተቱት ታዋቂ ሰዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው አርቲስት አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ)፣ ሌላኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሰአሊ ጁሊ ምሕረቱ ይገኙበታል፡፡
የአሜሪካ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ፣ አሜሪካዊቷ አቀንቃኝ ሰሊና ጎሜዝ፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ፣ የአሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተፎካካሪ ጆይ ባይደን እና የብላክ ሊቭስ ማተር መስራች አልሺያ ጋርዛ ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያውያኑ ከዝርዝሩ እንዲካተቱ ማን መረጣቸው?
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ከዝርዝሩ ሊካተቱ የቻሉት በቀድሞው የናይጄሪያ የፋይናንስ ሚኒስትር ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌአላ ጠቋሚነት ነው፡፡
የዓለም አቀፍ ክትባቶች ትብብር (Gavi) ሊቀመንበሩ ኢዌአላ በአሁኑ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት የኮቪድ-19 መልዕክተኛ ሆነው በመስራትም ላይ ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስን እጩ አድርገው ባቀረቡበት ጽሁፍ ዓለም አቀፉን ተቋም በመሩባቸው ዓመታት ያበረከቷቸውን አስተዋጽኦዎች ዘርዝረዋል፡፡
ለህክምና ግልጋሎቶች ፍትሃዊ ተደራሽነት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ሲታትሩ እንደነበር የገለጹ ሲሆን ኢቦላን ጨምሮ የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ ጠንካራ አመራር ሰጥተዋልም ብለዋል፡፡
አቤል ፖፕ የሙዚቃ ዘውግ ሚስጥራዊነት በላላበት ወቅት የተገኘ ሚስጥራዊ ሰው ነው ሲል በገለጸው እና በተወዳጁ እንግሊዛዊ ድምጻዊ ኤልተን ጆን ነው በዝርዝሩ እንዲካተት በእጩነት የቀረበው፡፡
ኤልተን የእሱን ጨምሮ የተወዳጇን ድምጻዊ የአስቴር አወቀን ስራዎች አጥብቆ የሚወደውን ወጣቱን ድምጻዊ ያደንቃል፡፡
ሰአሊ ጁሊ ምሕረቱ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ከባቢያዊ ጉዳዮችን አመስጥራ በስዕል ስራዎቿ በመከሰት ትታወቃለች፡፡
በትርጉም አዘል ስራዎቿ የራሷን ቋንቋ ለመፍጠር ትሞክራለች ሲል ባሞካሻት ዴቪድ አዣዬ ነው ለዝርዝሩ የታጨችው፡፡
ትውልደ ጋናዊው አዣዬ ከንግስቲቷ ሰር የሚል ማዕረግን ለመቀበል የበቃ እውቅ እንግዛዊ የአርክቴክቸር ባለሙያ ነው፡፡