በቲክቶክ የጽሁፍ መልዕክቶችን ማጋራት ሊጀመር ነው
የቻይናው ኩባንያ እጀምረዋለው ያለው አገልግሎት የማህበራዊ ሚዲያዎች ፉክክር መጠናከርን ያሳያል ተብሏል
ቲክቶክ ባለፈው ወር እንደ ስፖቲፋይ የሙዚቃ ስርጭት መጀመሩ ይታወሳል
የማህበራዊ ትስስር ገጾች ፉክክር በፌስቡክና ትዊተር ብቻ የተገደበ አይደለም።
በየቀኑ ከ1 ቢሊየን በላይ ተጠቃሚዎቹ ያሉት ቲክቶክም የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ ገበያውን ለመቆጣጠር እየሰራ ነው።
ቲክቶክ እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ሁሉ የጽሁፍ መልዕክቶችን ማጋራት የሚያስችል አማራጭ ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
የቻይናው ኩባንያ ተጠቃሚዎቹ በቅርቡ ግጥምም ሆነ አጫጭር ጽሁፎችን ከድምጽ ጋር በማዋሃድ ማጋራት ይችላሉ ብሏል።
ይህም በቪዲዮ እና ፎቶግራፍ ከሚለቀቁ ይዘቶች ባሻገር ጽሁፍ የሚመርጡ ደንበኞቹ ራሳቸውን እንዲገልጹና እንዲያስተዋውቁ እንደሚረዳቸው ነው የጠቆመው።
ቲክቶክ ባለፈው ወርም እንደ “ስፖቲፋይ” እና “አፕል ሚዩዚክ” የሙዚቃ ስርጭት መጀመሩ የሚታወስ ነው።
በቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ የሚተዳደረው ቲክቶክ በብራዚል እና ኢንዶኔዥያ “ቱክቶክ ሚዩዚክ” የተሰኘውን ሙዚቃዎችን መስማት እና ማውረድ የሚያስችል መተግበሪያ አገልግሎት አስጀምሯል።
በሲንጋፖር፣ ሜክሲኮና አውስትራሊያም አገልግሎቱን በከፊል የጀመረ ሲሆን፥ በሌሎች ሀገራትም የሙዚቃ መተግበሪያውን ለማስፋፋት ማቀዱን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ቲክቶክ በ2021 የአሜሪካውን ጎግል በመቅደም በአለማችን በርካታ ተጠቃሚ ያለው የኦንላይን ትስስር ገጽ መሆን መቻሉ ይታወሳል።