የአጫጭር ቪዲዮዎች ማጋሪያ የትስስር ገጹ በ2022 ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 85 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ተገልጿል
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በ2022 ከፍተኛ ትርፍ ማስመዝገቡ ተነግሯል።
ቲክቶክ በ2021 ካገኘው ትርፍ በ80 በመቶ ጭማሪ ያለው የ25 ቢሊየን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ፋይናንሽያል ታይምስ አስነብቧል።
የማስታወቂያ ገቢው በእጅጉ የጨመረለት ቲክቶክ ከቻይና ውጭ ባሉ ሀገራት ያገኘው ትርፍ 15 ቢሊየን ዶላር ነው ብሏል ዘገባው።
ቻይናውያን የቲክቶክ አምሳያ የሆነውን ዶይን የተሰኘ የባይትዳንስ መተግበሪያ በስፋት እንደሚጠቀሙ ይታወቃል።
ፋይናንሽያል ታይምስ ለኩባንያው ቅርበት ካላቸው ሰዎች አገኘውት ብሎ ስላጋራው መረጃ ባይትዳንስ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ባለፈው አመት የ300 ቢሊየን ዶላር ዋጋ የወጣለት ቲክቶክ በዚህ አመትም የአለማችን ውዱ የግል ንብረት ሆኖ መዝለቁ እየተነገረ ነው።
ኩባንያው ምንም እንኳን ትርፉ ቢመነደግም የመስራቹ ዣንግ ይሚንግ ሃብት በ13 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሎ 42 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
የቲክቶክ ስራ አስፈጻሚ ሹ ዚ ቸው በአሜሪካ ኮንግረንስ ቀርበው ካደረጉት ንግግር በኋላ የቢሊየነሩ ሃብት መቀነሱ ተነግሯል።
የቲክቶክ መስራቹ ዣንግ ይሚንግ እና የቀድሞው የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ ሊያንግ ሩቦ የቲክቶክ 20 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ነው የተገለጸው።
የአክሲዮን ድርሻውን ለአሜሪካውያን የማይሸጥ ከሆነ እንደሚታገድ በዋይትሃውስ ባለስልጣናት ማሳሰቢያ የደረሰው ቲክቶክ፥ እስካሁን በ12 ሀገራት በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ታግዷል።
በአሜሪካ ብቻ ከ150 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት የቪዲዮ ማጋሪያው ቲክቶክ ወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ከ3 ቢሊየን መሻገራቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ።
በአሜሪካም የባይደን አስተዳደር ቲክቶክን እዘጋለሁ በሚል ቢዝትም የበርካቶችን ስራ የሚነጥቅ በመሆኑ ተፈጻሚነቱ አጠራጣሪ ነው ይላሉ ተንታኞች።