
ቲክቶክ የተላለፈበትን ውሳኔ ለማስቀልበስ ያቀረበው ይግባኝ ውድግ ተደርጎበታል
ቲክቶክ በአሜሪካ ምድር ሊዘጋ ስንት ቀን ቀረው?
መሰረቱን በቻይን ያደረገው ቲክቶክ በአሜሪካ የደህንነት ስጋት ደቅኗል በሚል እንደሚታገድ ከወራት በፊት ውሳኔ ተላልፎበት ነበር።
የባይት ዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 170 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል።
ይህ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያ የአሜሪካዊያን ተቋማት እና ዜጎችን መረጃዎች ለቻይና አሳልፎ እየሰጠ ነው የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ይህን ተከትሎ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር ቲክቶክ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ደቅኗል በሚል ለአሜሪካዊያን ኩባንያዎች እንዲሸጥ አልያም እንዲታገድ በሚል ውሳኔ ተላልፎበታል።
ቲክቶክ በበኩሉ የቀረበበት ክስ ሀሰተኛ መሆኑን የመረጃ ማዕከሉ በቻይና ሳይሆን በአሜሪካ እንደሚገኝ ይህንንም ማሳየት እንደሚችል አስታውቋል።
በአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት የተላለፈው ይህ ውሳኔ በ90 ቀናት ውስጥ እንዲተገበርም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
በምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲሸጥ አልያም እንዲታገድ የሚፈቅደው የመጨረሻ ቀነ ገደብ ጥር 19 ቀን 2025 ላይ ይጠባቀቃል።
ባይት ዳንስ ኩባንያም ውሳኔውን ለማሻር በህግ እንደሚታገል በወቅቱ ገልጾ የነበረ ሲሆን ይህ አቤቱታው ውድቅ ተደርጎበታል።
በዚህም መሰረት ቲክቶክ ኩባንያ አሁንም እንዲታገድ አልያም እንዲሸጥ በሚል የተላለፈበት ውሳኔ ሊያበቃ አንድ ወር ገደማ ቀርቶታል።
ይሁንና ኩባንያው የመጨረሻው ቀን ከመድረሱ በፊት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥለው ለሀገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚል አስታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክ እንዲሸጥ አልያም እንዲታገድ ከአራት ዓመት በፊት ሞክረ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቆይቷል።
ይሁንና ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ተወዳድረው ድጋሚ የተመረጡት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቲክቶክን እንደማይዘጉ ተናግረዋል።
ይሁንና ቲክቶክ እንዲሸጥ አልያም በአሜሪካ እንዲታገድ በሚል የተላለፈው ውሳኔ ስልጣን ሊይዙ አንድ ቀን ሲቀራቸው እንዲፈጸም ያስገዳል።
ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ እንደ ጎግል እና መሰል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከጥር 20 ጀምሮ ቲክቶክን ለማገድ እንዲዘጋጁ ማሳወቁ ተገልጿል።