በታዋቂ ኩባንያዎችና ግለሰቦች የቲክቶክ አካውንት ላይ የሳይበር ጥቃት ተፈጸመ
ቲክቶክ ሲኤንኤንን ጨምሮ አካውንታቸው ከቁጥጥር ውጭ የሆነባቸውን አካላት እያገዘ መሆኑን አስታውቋል
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ የሳይበር ጥቃቱ እንዴትና በማን እንደተፈጸመ በዝርዝር አልገለጸም
ቲክቶክ በታዋቂ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን ገለጸ።
የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያው አካውንታቸው ከባለቤቶቹ ቁጥጥር የወጡ አካውንቶችን ለማስመለስ እየሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት በምን ያህል ሰዎች አካውንቶች ላይ የሳይበር ጥቃቱ እንደደረሰ አልገለጸም።
ጥቃቱ እንዴት እና በማን እንደተፈጸመም ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም።
የቲክቶክ አካውንታቸው የሳይበር ጥቃት ከተፈጸመባቸው መካከል የአሜሪካው የመገናኛ ብዙሃን ሲኤንኤን አንዱ ነው።
የቲክቶክ ቃልአቀባይ ሲኤንኤን ከቁጥጥሩ የወጣውን የቲክቶክ አካውንት ለማስመለስ ከባለሙያዎቹ ጋር እየሰራን ነው ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
በቲክቶክ ከ10 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን ማፍራት የቻለችው የቴሌቪዥን አቅራቢ ፓሪስ ሂልተን አካውንትም የሳይበር ጥቃት ሙከራ እንደተደረገበት ኩባንያው አስታውቋል።
በአሜሪካ ከ170 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ እንዲታገድ በሀገሪቱ ባለስልጣናት ጫናው በበዛበት ወቅት የሳይበር ጥቃት ዜናው መሰማት ለቻይናው ኩባንያ ፈታኝ ይሆናል ተብሏል።
ቲክቶክ የሳይበር ጥቃት ሙከራው “በጥቂት” የታዋቂ ግለሰቦችና የተቋማት አካውንቶች ላይ ያነጣጠረ ነው ከማለት ውጭ ማብራሪያ አለመስጠቱም ጥርጣሬ ፈጥሯል።
ቲክቶክ የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው የምትለው ዋሽንግተን፥ መተግበሪያው የአሜሪካውያን መረጃ ለቻይና ያጋራል የሚል ክስ ስታቀርብ ቆይታለች።
የአሁኑን የሳይበር ጥቃትም የመተግበሪያው የደህንነት ስርአት ጠንካራ እንዳልሆነ ማሳያ አድርጋ እያቀረበችው ነው።
ቲክቶክ በህዳር ወር 2024 በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም አንደኛው የፉክክር ሜዳ ከሆነ ሰነባብቷል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት ቲክቶክን ተቀላቅለው በአንድ ቪዲዮ ከ5 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን አፍርተዋል።
በቅርቡ ቲክቶክ ድርሻውን ለአሜሪካውያን ካልሸጠ ይታገድ የሚል ውሳኔ ያሳለፉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ቀደም ብለው በየካቲት ወር ቲክቶክን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 169 ቪዲዮዎችን ለቆ ያገኘው የተከታይ ቁጥር ግን 358 ሺህ ነው።፡
ቲክቶክ ወጣት መራጮን ለማግኘት ሁነኛው አማራጭ ይሆናል ብለው ያመኑት ባይደን እና ትራምፕ፥ የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ መተግበሪያን እያጣጣሉ መጠቀማቸውን ግን ቀጥለዋል።