የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስ መስራች በቻይና ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ
ዛንግ የአንደኛነቱን ቦታ የነጠቀው የታሸገ ውሃ ከሚያመርተው ባለሀብት ዞንግ ሻንሻን ነው ተብሏል
የባይትዳንስ መሰራቹ ዛንግ ይሚንግ በቻይና ቁጥር አንድ ሀብታም የሆነው በ49.3 ቢሊዮን ዶላር ነው
የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስ መስራች በቻይና ቁጥር አንድ ሀብታም ሆነ።
የባይትዳንስ መሰራች የሆነው ዛንግ ይሚንግ በ49.3 ቢሊዮን ዶላር ቁጥር አንድ የቻይና ባለሀብት መሆኑን አመታዊው የሀብታሞች ዝርዝር መረጃ ማሳየቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ በሪልኢስቴት እና በታዳሽ ኃይል የተሰማሩት አቻዎቹም ከፍተኛ ፉክክር አሳይተዋል።
ከባይትዳንስ ስራ አስፈጻሚነት በ2021 የለቀቀው የ41 አመቱ ዛንግ የሁሩን የቻይና የሀብታሞች ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ከታተመ ወዲህ በ26 አመት ውስጥ 18ኛው የቻይና ሀብታም ግለሰብ ለመሆን በቅቷል። ዛንግ የአንደኛነቱን ቦታ የነጠቀው፣ የሀብት መጠኑ በ24 በመቶ ቀንሶ 47.9 ቢሊዮን ዶላር ከሆነበት የታሸገ ውሃ ባለሀብቱ ዞንግ ሻንሻን ነው።
ምንም እንኳን ከቲክቶክ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ውስጥ የህግ ክርክር ቢያጋጥመውም፣ የባይትዳንስ አለምአቀፍ ገቢ ባለፈው አመት 30 በመቶ አድጎ 110 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን እና ይህም የዛንግ ሀብት መጠን እንዲጨምር እንደረዳው ሁሩን ገልጿል።
ሶስተኛ ደረጃ የያዘው ብዙም የማይታወቀው የቴንሴንት መሰራች ፖኒ ማ ሲሆን የፒዲዲ ሆልዲንግስ መሰራች የሆነው ኮሊን ሁዋንግ ደግሞ ባለፈው አመት ከነበረው የሶስተኛ ደረጃ ዝግ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በቻይና የቢሊየነሮች ቁጥር በ142 ቀንሶ 753 ደርሷል። ይህ በ2021 ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ከነበረው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከ1/3 በላይ ቀንሷል ተብሏል።
"ለቻይና ኢኮኖሚ እና ስቶክ ማርኬት ከባድ አመት ነበር" ሲሉ የሁሩን ሪፖርት ሊቀመንበር ሩፔርት ሁግወርፍ ተናግረዋል።
የከፍተኛ የሀብት ቅነሳ የታየው በቻይና ሪልኢስቴት ዘርፍ እንደሆነ የገለጹት ሁግወርፍ የኤሌክትሪክ ፍጆቻ እቃዎች ዋጋ በፍጥነት ማደጉን እና የዣኦሚ መስራች 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል። ሁግወርፍ እንዳሉት ከሆነ የሶላር ፖኔል፣ ሊቲየም ባትሪ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ሰሪዎች የገበያ ውውድሩ በመጠንከሩ ምክንያት አመቱ ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር።