በአሜሪካ የቲክቶክ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች ቁጥር 150 ሚሊየን ደረሰ
የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያው ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2020 ከነበረበት የ50 ሚሊየን ጭማሪ ማሳየቱንም ነው ቲክቶክ ያስታወቀው
የቻይናው መተግበሪያ የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው ያለችው አሜሪካ ቲክቶክ በመንግስት ተቋማት እንዳይከፈት እግድ ጥላለች
ቲክቶክ በአሜሪካ የወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር 150 ሚሊየን መድረሱን አስታወቀ።
ይህም በ2020 ከነበረው የ100 ሚሊየን ወርሃዊ ደንበኞቹ ቁጥር በ50 ሚሊየን ጭማሪ ማሳየቱን ነው ኩባንያው ይፋ ያደረገው።
የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሻው ዚ ከነገ በስቲያ ሃሙስ በአሜሪካ ኮንግረንስ የኢነርጂ እና ንግር ቋሚ ኮሚቴ ቀርበው ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ቲክቶክ የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው በሚል በበርካታ የመንግስት ተቋማት እንዳይከፈት እግድ ለጣለችው ዋሽንግተን ኩባንያቸው የመረጃ አያያዙ ምን እንደሚመስል ያብራራሉ ተብሏል።
የባይደን አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ቲክቶክ ለአሜሪካውያን የአክሲዮን ድርሻ የማይሸጥ ከሆነ መተግበሪያው ሙሉ በሙሉ እንደሚታገድ ማሳሰቡ ይታወሳል።
የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክርቤት የደህንነት ኮሚቴ ሊቀመንበሩ ማርክ ዋርነር፥ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ባወጣው ህግ የሚተዳደር ኩባንያ ውስጥ የሚቀመጥ መረጃ ደህንነቱ እጅግ አጠራጣሪ ነው ይላሉ።
ዋርነር የባይደን አስተዳደር በቲክቶክ ላይ ጠበቅ ላይ እርምጃ መወሰድ እንዲችል ተጨማሪ ስልጣን የሚሰጥ ህግን ለማውጣትም ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር እየሰሩ ነው ተብሏል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ከ1 ቢሊየን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚ ያለው ቲክቶክ ግን “የአሜሪካውያንን መረጃ ለስለላ ሊጠቀምበት ይችላል” የሚለውን ክስ አይቀበለውም።
ኩባንያው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መድቦ የመረጃ ደህንነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን በመግለጽም፥ የኩባንያውን ባለቤቶች መለወጥ (አክሲዮን ሽያጭ) የመረጃ ደህንነትን አያረጋግጥም ይላል።
ቲክቶክ በቅርቡ የአውሮፓ ደንበኞቹን መረጃ በየሀገራቱ ማከማቸት እንደሚጀምር ማሳወቁ ይታወሳል።
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ይፋ ካደረገው የአሜሪካ ወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር የወጣቶቹ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ጊና ራይሞንዶ ለብሉምበርግ ተናግረዋል።
ይህም ቲክቶክ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ከወጣቶች ጋር እንዳያቆራርጣቸው ስጋትን እንደሚፈጥር ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።