አሜሪካ ቲክቶክ ድርሻ ካልሸጠላት እገዳ እንደምትጥልበት ዛተች
ቲክቶክ ከ100 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ተጠቃሚዎች አሉት
ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጀምሮ ቲክቶክ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው በሚል በዋሽንግተን ጫና በርትቶበታል
የባይደን አስተዳደር ቻይናውያን ባለቤቶች በታዋቂው የቪዲዮ መተግበሪያ ቱክቶክ ላይ ያላቸውን ድርሻ እንዲቀንሱ ጠይቋል።
ይህ ካልሆነ ግን ቪዲዮ መተግበሪያ ላይ አሜሪካ እገዳ እንደምትጥል አሳውቃናለች ሲል ኩባንያው ለሮይተርስ ተናግሯል።
- አሜሪካ በመንግስት ተቋማት ቲክቶክ መጠቀምን ልታግድ ነው
እርምጃው ቲክቶክ የአሜሪካ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግስት ሊያስተላልፍ ይችላል የሚል ፍራቻ ባሳዩ የአሜሪካ ባለስልጣናት እና የህግ አውጭዎች ከተከታታይ አቋም አንዱ ነው ተብሏል።
ባይትዳንስ የተባለው ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ከ100 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ተጠቃሚዎች አሉት።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቲክቶክ ላይ እገዳ ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ያለው ለመጀመሪያ ጊዜ ነውም ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሦስት ዓመት በፊት ቲክቶክን ለማገድ ሞክረው የነበረ ሲሆን፤ የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ውድቅ አድርገውት ነበር።
የቲክቶክ ቃል አቀባይ ብሩክ ኦበርዌተር እንደተናገሩት ኩባንያው በቅርቡ በአሜሪካ ግምጃ ቤት በሚመራው የውጭ ኢንቨስትመንት ኮሚቴ ድርሻውን እንዲሸጥ ተጠይቋል።
ይህ ካልሆነ ግን ክስ እንደሚገጥማቸው አሳውቀውናል ነው ያሉት።
ችግሩ ብሄራዊ ደህንነትን መጠበቅ ላይ ከሆነ ድርሻ ማዛወር ችግሩን አይፈታውም ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ባይትዳንስ 60 በመቶው አክሲዮን በዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ 20 በመቶው በሰራተኞች እና 20 በመቶው በመስራቾቹ የተያዘ እንደሆነ ተነግሯል።