ቲክቶክ ለአውሮፓ አዲስ የመረጃ ደህንነት ስርዓትን ይፋ አደረገ
አሜሪካና አውሮፓ የተጠቃሚዎች መረጃ በቻይና መንግስት ይመነተፋል በሚል ቲክቶክ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው
ኩባንያው የአውሮፓ ሀገራት ደንበኞቹን መረጃ በየሀገራቱ ማከማቸት እንደሚጀምር ተናግሯል
ቲክቶክ ከህግ አውጭዎች የሚደርስበት ግፊት እየጨመረ በመምጣቱ “ፕሮጄክት ክሎቨር” የሚል ቅጽል ስም ያለው አዲስ የመረጃ ደህንነት አስተዳደር አስታውቋል።
የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በቅርቡ የመንግስት ሰራተኞች በስልካቸው ቲክቶክ እንዳይጠቀሙ አግደዋል።
እገዳው የተጣለው በቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ባለቤትነት የተያዘው ቲክቶክ፤ የቻይና መንግስት የተጠቃሚዎችን መረጃ በመሰብሰብ ጥቅም ላይ ሊያውል ይችላል የሚለው ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋይትሀውስ በቻይና ባለቤትነት የተያዘውን የቪዲዮ መተግበሪያ ቲክቶክ እና ሌሎች በውጭ ሀገር የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች፤ ብሄራዊ የደህንነት ስጋቶችን የሚፈጥሩ ከሆነ ለአስተዳደሩ እርምጃ እንዲወስድ አዲስ ስልጣን የሚሰጠውን ህግ ደግፏል።
ቲክቶክ በሰጠው መግለጫ፤ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የአውሮፓ ደንበኞቹን መረጃ በየሀገራቱ ማከማቸት እንደሚጀምር ነው ያስታወቀው።
የዚህ እርምጃ አካል ነው የተባለው የአየርላንድ የመረጃ ማዕከል በቅርቡ እንደሚከፍትም ገልጿል።
የመረጃ ማዕከላቱ የሚተዳደሩት በሦስተኛ ወገን መሆኑም የሚነሳውን ስጋት እንደሚቀንሰው ታምኗል።
ቲክቶክ በአሜሪካም ተመሳሳይ ስልት እንደሚጠቀም መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኩባንያው በጠላትነት የፈረጁትን የአሜሪካ ህግ አውጭዎችን ለማሳመን “ፕሮጄክት ቴክሳስ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ስራ ይሰራል ተብሏል።