ልዩልዩ
ሴኔጋል ቲክቶክን ካገደች በኋላ ቁጥጥር ላይ ስምምነት እንዲደረግ ጠየቀች
ሀገሪቱ የቲክቶክ አካውንቶችን ማገድ የሚያስችል ስምምነት እንዲፈርም አቋም ይዛለች
ሴኔጋል ባለፈው ነሀሴ "ሀሰተኛና የክህደት መልዕክቶች" እየተሰራጨበት ነው በሚል ቲክቶክን አግዳለች
የሴኔጋል ባለስልጣናት ቲክቶክ ላይ የጣሉትን እግድ ለማንሳት አሻፈረኝ ብለዋል።
ባለስልጣናቱ ተወዳጅነትን ያተረፈው የቪዲዮ መለዋወጫ ባለቤት የሆነው ኩባንያ አካውንቶችን ማገድ የሚያስችል ስምምነት እንዲፈርም አቋም ይዘዋል።
የሀገሪቱ የኮሚኒኬሽን ሚንስትር ለጊዜው የቲክቶክ እግድ ባለበት እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ጠቅለል ያለ የጽሁፍ ስምምነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሚንስትሩ አክለውም የሀገሪቱ ሹማምንት ከቲክቶክ ጋር ንግግር ላይ ናቸው ብለዋል።
በሁለቱ ወገኖች ንግግር የሴኔጋል መንግስት የተሻለ የቁጥጥር ስርዓት መጠየቁ ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ለይዘት ፈጣሪዎች ፍትኃዊ የክፍያ ስርዓት በመዘርጋት ወጣቶች ከማህበራዊ ትስስር ስራ ገቢ እንዲያገኙ ጠይቋል።
ሴኔጋል ባለፈው ነሀሴ "ሀሰተኛና የክህደት መልዕክቶች" እየተሰራጨበት ነው በሚል ቲክቶክን የሀገሪቱን መረጋጋት አስግቷል ስትል አግዳለች።
በሰኔ ወር በፕሬዝዳንት ሚኪ ሳሌና በተቃዋሚያቸው ኦስማን ሶንኮ መካከል የነበረው ፍትጊያ ወደ ግጭት አምርቶ በአፍሪካ ሰላማዊ የሚል ዝና የነበራትን ሀገር ስም መክሰሙ ተነግሯል።