የአሜሪካ ኮንግረንስ አባላት ለቲክቶክ ስራ አስፈጻሚ ያነሷቸው ፈገግ የሚያሰኙ ጥያቄዎች
የኮንግረንስ አባላቱ ከቴክኖሎጂው አለም የራቁ መሆናቸውን የሚያሳብቁት ጥያቄዎች በርካታ አስቂኝ ቪዲዮዎች እየተሰራባቸው ነው
አሜሪካ፥ ቲክቶክ በቻይና መንግስት ለስለላ ሊውል ይችላል በሚል ብሄራዊ የደህንነት ስጋቴ ነው ብላለች
የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹ ቸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአሜሪካ ኮንግረንስ የኢነርጂ እና ንግር ኮሚቴ በመገኘት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
150 ሚሊየን አሜሪካውያን ተጠቃሚ ያለው ቲክቶክ ብሄራዊ የደህንነት ስጋቴ ነው ያለችው ዋሽንግተን በኮንግረንስ አባላቷ የተነሱ ጥያቄዎች ግን በመላው አለም ትዝብት ውስጥ ከቷታል።
የኮንግረንስ አባላቱ ያነሷቸው ፈገግ የሚያሰኙ ጥያቄዎችም ፖለቲከኞቹ ምን ያህል ከቴክኖሎጂው አለም መራቃቸውን ያሳያል የሚሉ አስተያየቶች ተበራክተዋል።
የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ለአስቂኝ ጥያቄዎቹ የስላቅ ምላሽን መስጠታቸውንም ቀጥለዋል ነው የሚለው የሲ ኤን ኤን ዘገባ።
አነጋጋሪ ጥያቄ በማንሳት የኖርዝ ካሮሊናውን ተወካይ ሪቻርድ ሁድሰን የሚደርስባቸው አልተገኘም።
ሁድሰን “በቤቴ ውስጥ ዋይፋይ ካለና ቲክቶክ ከጫንኩ ቲክቶክ የዋይፋይ ኔትወርኩን ይጠቀማል ወይ” የሚል ጥያቄን አንስተዋል።
የቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚውም ይመልሳሉ፤ “ዋይፋዩን ከከፈቱት.. አዎ” የሚል ምላሽ።
አንድ የቲክቶክ ተጠቃሚ ሁድሰንን “ቲክቶክ ስከፍት መተግበሪያው የኤሌክትሪክ ሃይል ለመስረቅ ባትሪዬን ይጠቀም ይሆን?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ተሳልቆባቸዋል።
“ስልኬን ቻርጅ እያደረኩ ቲክቶክ ከከፈትኩ ብሄራዊ የሃይል ቋቱን መቆጣጠር እችላለሁ? ፤ ስልኬን ኤርፕሌን ሞድ ላይ ባደርገው ስልኬ የሚበር አውሮፕላንን ይቆጣጠራል ወይ” የሚሉና ሌሎች ፈገግ የሚያሰኙ ጥያቄዎችም በቲክቶክ ቪዲዮ እየተሰራባቸው ተለቀው ሚሊየኖች ተቀባብለዋቸዋል።
ጆርጂያን የወከሉት በዲ ካርተር ለቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሹ ቸው ያነሱት ጥያቄም “የአሜሪካ ኮንግረንስ የእድሜ ገደብ ሊኖረው ይገባል” አስብሏል።
ካርተር “ቲክቶክ የተጠቃሚዎቹን እድሜ እንዴት ነው የሚለየው? አይናቸውን አይቶ ነው አይደል?” የሚል ጥያቄን ያነሳሉ።
በኮንግረንስ አባሉ ጥያቄ መገረሙ በግልጽ የሚታየው ቸው፥ ቲክቶክ የሰዎችን መልክ፣ አይን ወይም ድምጻቸውን በመጠቀም የተጠቃሚዎቹን ማንነት አይለይም፤ የፊት ገጽታን የሚጠቀመው ለፊልተር ብቻ ነው፤ ተጠቃሚዎቹ አካውንት ሲከፍቱ እድሜያቸውን ራሳቸው ሊሞሉ ይችላሉ” የሚል ምላሽ ይሰጣል።
በምላሹ ያልረኩትና ስለፊልተር ግንዛቤው የሌላቸው ካርተር ግን “አይናችን አይታችሁ እድሜያችን ለማወቅ ካልፈለጋችሁ በስተቀር አይናችን የት እንዳለ ማወቅ ም ይሰራላችኋል?” የሚል ሌላ አስቂኝ ጥያቄ ያስከትላሉ።
ይህ የኮንግረንሱ አባል ያነሱት ጥያቄ እና የተሰጣቸው መልስ በቲክቶክ ሚሊየኖች የተቀባበሉትና ሳቅና ጨዋታ የፈጠሩበት ጉዳይ ሆኗል።
የካርተር ቃል አቀባይ ግን ቲክቶክ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት ነው በመባሉ ካርተር ቲክቶክ ስለማይጠቀሙ መነጋገሪያ የሆነውን ጥያቄ ሊያነሱ ችለዋል በሚል ለመከላከል ሞክረዋል።
አሜሪካውያን በቀጥታ በተላለፈው የኮንግረንስ ስብሰባ የወከሏቸው ሰዎች ከዘመኑ ቴክኖሎጂ የተራራቁ መሆናቸውን ተመልክተዋል የሚለው የቴክ ክራንች ዘገባ፥ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት ሆኗል የተባለው ቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ራሱ በሁኔታው ሳይገረሙ እንዳልቀሩ ይገልጻል።
ክርስቲያን ዳይን የተባለ የቲክቶክ ተጠቃሚም “አልጎሪዝም ምን አይነት ቀለም አለው?” በሚል በለቀቀው ቪዲዮ የኮንግረንስ አባላቱ ቲክቶክም ሆነ ሌሎች መተግበሪያዎች እንዴት እንደሚሰሩ ግንዛቤ እንደሚጎድላቸው አሳይቷል።
ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በተመለከቱት የዳይን ቪዲዮ ስር የሰፈሩ አስተያየቶችም ፈገግታን የሚያጭሩ ናቸው።