የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ የሀገሪቱ ዶክተሮች ጥሪ አቀረቡ
ኦሎምፒኩ እንዲሰረዝ የሚጠይቀው የኢንትርኔት የፊርማ ማሰባሰቢያ ላይ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፈርመዋል
ጃፓን የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክን በጥብቅ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች
6 ሺህ ዶክተሮችን የሚወክለው የቶክዮ የጤና ባለሙያዎች ማህበር በጃፓን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ ጥሪ አቅርቧል።
የጤና ባለሙያዎች የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ በምክንያትነት ያቀረቡት ኮቪድ 19 እንደሆነ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የቶክዮ ዶክተሮች ማህበር እንዳስታወቀው “የ2020 አሎምፒክን በሚያስተናግዱ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች አሁን ላይ በሙሉ አቅማቸው ታማሚዎችን እያስተናገዱ ነው፡፡ ከኦሎምፒክ ጋር ተያይዞ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካገረሸ ለታማሚዎች ምንም አይነት ቦታ የለም” ብሏል።
ማህበሩ ለጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ በጻፈው ደብዳቤ “የጃፓን ባለስልጣናት አሁን ባለው ሁኔታ ኦሎምፒክን ማካሄድ ከባድ እንደሆነ እና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤን ሊያሳምኑ ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል።
የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ የሚጠይቀው የኢነተርኔት (ኦንላይን) የፊርማ ማሰባሰቢያ ላይም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈረማቸው ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂዴ ሱጋ በበኩላቸው ኮቪድ 19 መከላከያዎችን በአግባቡ በመከተል ደህንነቱ የተጠበቀ ኦሎምፒክ ማካሄድ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው ተብሏል።
ጃፓን በፈረንጆቹ ከሐምሌ 23 እስከ ነሃሴ 8/2021 እንደሚካሄድ መርሃ ግብር የወጣለትን ኦሎምፒክ በጥብቅ የኮቪድ 19 መከላከያ ፐሮቶኮል ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ሆኖም ግን የበርካታ ሀገራት አትሌቶች በዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ኦሎሚክን ማካሄድ አሳሳቢ መሆኑን እየተናሩ ነው።