ከፍንዳታና ጨረሮች የሚጠብቁ መጠለያዎቹ 44 ሽህ ዶላር እየተሸጡ ናቸው
የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ነዋሪዎች የቦምብ መጠለያ መግዛት ጀመሩ
ሰሜን ኮሪያ በጥቅምት ወር ጃፓን ላይ ሚሳይል መተኮሷን ተከትሎ ጃፓናዊያን በህይወት ለመቆየት መላ ያሉትን እየሞከሩ ነው ተብሏል።
ከጥቃቱ በኋላ በተንቀሳቃሽ ስልክ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያዎችን ያወጣችው ጃፓን፤ እንደ ሜጉሚ ሞሮሆሺ ያሉ ዜጎቿ ውሳኔ ወስነዋል። ይህም የቦምብ መጠለያ መግዛት ነው።
ሮይተርስ እንደዘገበው ሞሮሆሺ በጃፓን በየጊዜው የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አሳስቧት ቤቷን ለሦስት ልጆቿ በሚሆን መልኩ ማስፋፋት ትፈልግ ነበር። ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ ሚሳይሎች ዛቻ አጣዳፊ የሆነ እርምጃ እንድትወስድ አሳምኗታል።
በፖለቲካ ውጥረቱ ጥላ ውስጥ የሞሮሆሺ ቤተሰብ ደህንነታቸውን በእጃቸው ከወሰዱት ጃፓናውያን መካከል ናቸው ያለው ሮይተርስ፤ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷልም ብሏል።
"የቀውስ-አንድ" መጠለያዎችን እየሸጠ የሚገኘውን ናኦ ኢንጂነሪንግ የተባለ ኩባንያ ከፈረንጆቹ ታህሳስ 2021 ጀምሮ ፍላጎት እንደጨመረ ተናግሯል። ነገር ግን ኩባንያው በየካቲት ወር የሩሲያና ዩክሬንን ከተቀሰቀሰ በኋላ በጥያቄዎች መብዛት ተመልክቻለሁ ብሏል።
ጃፓን ከ70 ዓመታት በኋላም ቢሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የአቶሚክ ፍንዳታዎችን ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጸመው ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ትዝታዎችን እየኖረች ነው።
በቅርቡ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸውን ለመከላከያ "ሁሉንም መንገድ" እንጠቀማለን ካሉ በኋላ የኒውክሌር ስጋትን እንደገና ተቀስቅሷል ነው የተባለው።
ሆኖም የዓመቱ የጃፓን ከፍተኛ ስጋት ደሴቶች ላይ የወደቁት ሰሜን ኮሪያ በደርዘን የሚቆጠሩ ሚሳይሎች ናቸው።ፒዮንግያንግ እ.አ.አ ከ2017 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆንም ለቶኪዮ ስጋትን አንጃቧል።
በቅርቡ የሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይል ከሰሜን ምዕራብ የባህር ጠረፍ 200 ኪሎ ሜትር ማረፉ ይታወሳል። የናኦ ኩባንያ መጠለያዎች ከብረት የተሰሩ ሲሆኑ ከሚሳይል ወይም ከኒውክሌር ፍንዳታ በቀጥታ ካልተመታ በቀር ሁሉንም የሚቋቋም ነው ተብሏል።
የመጠለያው እስራኤል ሰራሽ የማጣሪያ ዘዴ ጨረሮችን ወይም አደገኛ ጋዝን ይከላከላልም ተብሏል። ነገር ግን ይህ ጥበቃ ዋጋው ሰማይ መሆኑን ነው ሮይተርስ የዘገበው።
ከቶኪዮ በስተሰሜን በሚገኘው ኢባራኪ ግዛት በሚገኘው የናኦ ፋብሪካ የተገነቡት መጠለያዎቹ ከተከላ በፊት 44 ሽህ ዶላር (ስድስት ሚሊዮን የን) ይሸጣል።