ወላጆች የስም ለውጡን የማያደርጉ ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ተነግሯል
ሰሜን ኮሪያ ወላጆች የልጆቻቸው ስም የሀገር ፍቅርን በሚያንፀባርቅ መልኩ እንዲያስተካክሉ አዘዘች።
የሀገር ፍቅርን ያንፀባርቃሉ የተባሉት ስሞች ግን "ቦምብ"፣ "ጠመንጃ" እና መሰል ወታደራዊ ትርጉም ያላቸው ናቸው።
ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደም የመጨረሻ ፊደላቸው ለስለስ ያሉ ስሞችን መጠቀም ፈቅዳ ነበር።
በዚህም እንደ ኤሪ (ተወዳጅ ወይም ፍቅር የሚል ትርጉም ያለው) እና ሱ ሚ (የውብዳር ወይም ውበቱ) የሚሉና ፍቅርና ውበትን የሚገልፁ ስሞች በብዛት ጥቅም ላይ ሲውሉ ታይቷል።
አሁን ግን የሀገሪቱ መንግስት እነዚህ ስያሜዎች ጦር ጦር ሊሸቱ ይገባል ብሏል።
የሰሜን ኮሪያን ርዕዮተ አለማዊ አስተሳሰብና ወታደራዊ ዝግጁነት የማያሳዩ ናቸው የተባሉት ስሞችም በአዳዲስ አብዮታዊ ስያሜዎች ይቀየሩ ዘንድ ለወላጆች መመሪያ ተላልፏል ነው የተባለው።
የስም ለውጡ የልጆቹን ብቻ ሳይሆን የወላጆቻቸውን ወይም የአባታቸውንም ያካትታል። ወላጆች የስም ለውጡን የማያደርጉ ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ተነግሯል።
በአማራጭነት የቀረቡት ቹንግ ኢ (ሽጉጤ እንደማለት)፣ ፖክ ኢ (ቦምቡ ወይም ቦምቢት)፣ ኡይ ሶንግ (ሳተላይት)፣ ቹንግ ሲም (ታማኝ) እና የመሳሰሉ ከፒዬንግያንግ መገለጫዎች ጋር የተያያዙ ናቸው።
ለሬዲዮ ፍሪ ኤስያ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሀገሪቱ ዜጋ፥ "የሀገሪቱ መንግስት ያሳለፈውን የስም ቅያሬ በርካታ ሰዎች እየተቃወሙት ነው" ብለዋል።
በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ሁሉም ወላጅ የልጆቹን ስም ፓለቲካዊ ትርጉም እንዲኖረው እንዲያደርግ የተቀመጠው ቀነ ገደብ አንድ ወር ብቻ ቀርቶታል።
በርካቶችንም ይህን የሰሜን ኮሪያ መንግስት ውሳኔ መቃወማቸውን ነው ስማቸው ያልተጠቀሰ የሀገሪቱ ዜጋ የተናገሩት። በደቡብ ኮሪያ ተወዳጅ የሆኑ ስሞችን መጠቀምም በጥብቅ ተከልክሏል፤ የምዕራባዊያንን ባህል እንደሚያንፀባርቁ በማመን።
ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደምም ከቻይና፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የተወረሱ ናቸው ያለቻቸውን ስሞችን መጠቀም መከልከሏ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ርዕዮተ አለማዊ እሳቤዬን እና ወታደራዊ ዝግጁነቴን በስሞችም ካላየሁት እያለች ነው።
በርግጥ በኢትዮጵያ ወታደራዊ መንግስት በሚያስተዳድርበት ጊዜ ፍቅር በቦምብ ይገለፅ ነበር (ቦምቡ ፍቅርሽ ሲፈነዳ... )። በወቅቱ አብዮት የሚለው ስምም የበርካታ ኢትዮጰያውያን መጠሪያ መሆኑ ይታወሳል።