የጃፓን ደጋፊዎች ሀገራቸው ከዓለም ዋንጫ ውጪ ብትሆንም ስታዲየም ማጽዳታቸውን ቀጥለዋል
ጃፓን በትናትናው እለት በፍጹም ቅጣት ምት በክሮሺያ ተሸንፋ ከዓለም ዋንጫ ውጪ ሆናለች
የጃፓን ደጋፊዎች ከሀገራቸው ውጪ የሌላ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ሲመለክቱም ስታዲየም ያጸዳሉ
በአነጋጋሪነቱ እና ባልተጠበቁ ውጤቶች በታጀበው የኳታር የዓለም ዋንጫ ላይ የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች በመልካም ስራ በበርካቶች ዘንድ እየተደነቁ ነው።
በኳታር የዓለም ዋንጫ 2010 እና 2014 የዓለም ዋንጫ አሸናፊዎች የነበሩትን ጀርመንን እና ስፔንን መርታት ጥሎ ማለፍን ተቀላቅላ የነበረችው ጃፓን በትናትናው እለት ከዓለም ዋንጫ ውጪ ሆናለች።
ትናንት በጃፓን እና ከብሮሺያ መካከል በተደረገ የጥሎ ማፍ ጨዋታ ጃፓን በፍጹም ቅጣት ምት በክሮሺያ በመረታቷ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ሳትችል ቀርታለች።
ጃፓን ተሸንፋ ከዓለም ዋንጫ ውጪ ብትሆንም በኳታር ተገኝተው ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ የጃፓን ደጋፊዎችም ሀዘናቸውን ያዝ አድርገው የዘወትር ተግባራቸውን ከመፈጸም አልቦዘኑም።
የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከጨዋታው መጀመር በፊት ቆሻሻ ለመሰብሰብ ይዘው በገቡት ፌስታል ውስጥ የጨዋታው ተመልካቾች ተጠቅመው የጣሉትን ቆሻሻዎች ሲሰበስቡ ተስተውሏል።
በዚህም የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች በሀዘን ውስጥ ሆነውም ቢሆን ስታዲየም የማጽዳት መልካም ተግባራቸውን ለዓለም አስተምረው ወጥተዋል።
የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ከዚህ ቀደምም ሀገራቸው ጀርመንን እና ስፔንን የረታችበት ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ስታዲየም ሲያጸዱ መታየታቸው አይዘነጋም።