በትራምፕ ፖሊሲ በርካታ ዜጎቻቸው የሚባረሩባቸው የአፍሪካ ሀገራት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ህገ ወጥ ስደተኞችን ለማስወጣት በያዙት ፖሊሲ ከ41 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ወደ መጡበት ይመለሳሉ ተብሏል
በዚህ ሂደት ውስጥ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ከ1,700 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተካተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞችን ከሃገር ለማስወጣት ያስጀመሩት ዘመቻ ህጋዊ እውቅና የሌላቸው በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የድንበር ደህንነትን ለማስጠበቅ እና የህገወጥ ስደተኞችን ፍልሰት ለማስቆም ያለመ ጠንካራ ትዕዛዞችን በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ፖሊሲ በስደተኞች ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ ስጋትን ያስከተለ ሲሆን የጅምላ ማስወጣት ሂደቱ ብዙ ቤተሰቦችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ ከማህበረሰቡ ጋር ጥልቅ ግንኙነት ያላቸውን የረጅም ጊዜ ነዋሪዎችን ጨምሮ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ስለማሳደሩ እየተነገረ ነው።
ከአፍሪካ እንደ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ሶማሊያ እና ሴኔጋልን ከመሳሰሉ ሀገራት የመጡ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች የመባረር ስጋት ገጥሟቸዋል።
ከ1980 ጀምሮ በአሜሪካ ውስጥ ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር በ16 እጥፍ ያደገ ሲሆን ይህ ቁጥር በየጊዜው ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ቀጥሏል፡፡
እንደ ማይግሬሽን ፖሊሲ ኢንስቲትዩት መረጃ በ2019 2.1 ሚሊየን የሚጠጉ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ ስደተኞች በአሜሪካ ውስጥ ይኖራሉ ፤ ይህም ከጠቅላላው 44.9 ሚሊዮን የውጭ ሀገር ተወላጆች ቁጥር 5 በመቶ የሚሸፍን ነው።
በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት 4.6 ሚሊዮን ጥቁር ስደተኞች አብዛኛዎቹ ከካሪቢያን የመጡ ሲሆኑ፤ ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካውያን እያደገ የመጣውን የጥቁር ስደተኞች ክፍል ይወክላሉ።
የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ አጠቃላይ የውጭ ሀገራት ተወላጅ የጥቁሮች ቁጥር በ2060 ከእጥፍ በላይ እንደሚጨምር እና ወደ 9.5 ሚሊዮን እንደሚደርስ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
በአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ (አይሲኢ) አመታዊ ሪፖርት መሰረት በ 2024 ወደ 1,818 የሚጠጉ አፍሪካውያን ዜጎች ከሀገሪቱ ሲባረሩ ሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ እና ናይጄሪያ በዝርዝሩ ውስጥ ቀዳሚ ሆነዋል።
እ.ኤ.አ. ከህዳር 2024 ጀምሮ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያ (አይሲኢ) ከሀገር የሚያስወጣቸውን ከ1 ሚሊየን 445 ሺህ በላይ ህገ ወጥ ስደተኞች የመጨረሻ ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳን እነዚህ ግለሰቦች እስካሁን ያልታሰሩ ወይም በማቆያ ጣብያዎች ውስጥ ያልገቡ ቢሆንም ወደፊት ሊባረሩ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፤ ይህም በነዚህ ዜጎች ውስጥ ያለውን እርግጠኛ አለመሆን እና ጭንቀት አባብሶታል፡፡
ከዚህ ውስጥ 41,323 ህገወጥ አፍሪካውያን ስደተኞች የተካተቱ ሲሆን ከአጠቃላይ ቁጥሩ ደግሞ 2.86 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡
ይፋ በተደረገው ዝርዝር ውስጥ 4,090 ዜጎቿ የሚባረሩባት ሶማሊያ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች፡፡
ማውሪታንያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ጊኒ እና ካሜሩን ከሁለት እስከ ስድስት በሚገኝው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በ7ተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝው ኢትዮጵያ በበኩሏ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ከ1,700 በላይ ዜጎቿ ከአሜሪካ የሚባረሩባት ይሆናል፡፡