የጋዛ ፍርስራሽ ተጸድቶ እስከሚያልቅ ድረስ ጎረቤት ሀገራት ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ ዶናልድ ትራምፕ ጠየቁ
አሜሪካ ከአረብ ሀገራት ጋር በመተባበር የፈራረሱ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት አቅዳለች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በ15 ወራት ጦርነት የጋዛ 60 በመቶ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ15 ወራቱ ጦርነት በፍርስራሽ የተሞላውን ጋዛ ሙሉ ለሙሉ ለማጽዳት የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲዘዋወሩ ጠየቁ፡፡
ግብፅ እና ዮርዳኖስ ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ ሀሳብ ያቀረቡት ትራምፕ ጥያቄውን ለዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ ማቅረባቸውን እና በቅርቡ የግብፁን ፕሬዝዳንት ለመጠየቅ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
በትራምፕ “የፍርስራሽ ሜዳ” በሚል የተገለጸችውን ጋዛ አጽድቶ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ቢያንስ አንድ ሚሊየን የሚሆኑ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲዛወሩ ነው የተጠየቀው፡፡
እነዚህ ዜጎች በጎረቤት ሀገራት የሚኖራቸው ቆይታ በጊዜያዊነት አልያም ለረጅም ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ያቀረቡት ሀሳብ በሀማስ እና በፍልስጤም አስተዳደር ተቀባይነት አላገኘም፤ ግብጽ እና ዮርዳኖስም ሀሳቡን ተቃውመዋል፡፡
ትራምፕ ጥያቄውን በይፋ ለግብፅ አቅርበው ይሁን አይሁን ግልፅ ባይሆንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ "በስፈራ ፍልስጤማውያንን በጊዜያዊነትም ሆነ ለረጅም ጊዜ ከመሬታቸው ማስለቀቅ ተቀባይነት የለውም” ሲል ተቃውሞውን ገልጿል፡፡
ሀማስ በበኩሉ “የጋዛ ነዋሪዎች ለ15 ወራት ሞት እና መከራ እየተቀበሉ ከአካባቢያቸው ሳይለቁ ቆይተዋል አሁን ለመልሶ ግንባታ በሚል ምክንያት ቀያቸውን አይለቁም” ብሏል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በንግግራቸው “ሁሉም ነገር ፈርሷል ማለት ይቻላል፤ ከአንዳንድ የአረብ ሀገራት ጋር በመተባበር አዳዲስ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት እየተዘጋጀን ነው” ብለዋል፡፡
ለ15 ወራት በዘለቀው ጦርነት ከ47 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ሚሊዮን ሁሉም የጋዛ ነዋሪዎች በሚባል ደረጃ ተፈናቅለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ቀደም ሲል ባወጣው ሪፖርት በጋዛ ዙሪያ ያሉ ህንጻዎች ፣ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተልማቶች ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ መውደማቸውን እና ለመገንባት አስርተ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡