ትራምፕ እገዛዋለሁ ባሉት ግሪንላድ እስራኤላውያንን ማስፈር ይችላሉ -ኢራን
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጋዛ ፍርሽራሽ ተጸድቶ እስኪያልቅ ድረስ ፍልስጤማውያን በጎረቤት ሀገር እንዲሰፍሩ በቀረበው ሀሳብ ላይ ተሳልቀዋል
ሚኒስትሩ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሀማስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ሆኖ ይወጣል ብለዋል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ የጋዛ ፍርሽራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን ወደ ዮርዳኖስ እና ግብጽ እንዲዘዋወሩ ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት ሀሳብ ላይ ተሳልቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ትራምፕ “ከፍልስጤማውያን ይልቅ እስራኤላውያንን እገዛዋለሁ ወዳሉት ግሪንልንድ ለምን አይልኩም፤ በዚህ መንገድ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይመታሉ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አባስ አርጋቺ ትራምፕ ወደ ኋይት ሀውስ ከተመለሱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቀጠናዊ ጉዳዮችን ፣ የእስራኤል እና ትራምፕ ጥምረት ፣ የኒዩክሌር ፕሮግራም እና ሀማስን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ኒዩክሌር ተቋሞችን ለማጥቃት የሚያስቡ ከሆነ በአካባቢው ከባድ ቀውስ የሚያስከትል "የእብድ ውሳኔ" ይሆናል ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
“በኒዩክሌር ተቋማችን ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት አፋጣኝ እና ከፍተኛ ምላሽ እንደሚያስከትል በተደጋጋሚ አቋማችንን ግልፅ አድርገናል፤ ይህን እብደት እነሱም (አሜሪካ እና እስራኤል) ያደርጉታል ብዬ አላምንም፤ የሚሆን ከሆነ ግን መላውን ቀጠና ወደ አስከፊ ጥፋት የሚያስገባ እብደት ነው” ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት ለመውጣት ያሳለፉት ውሳኔ ቴሄራን የተቀመጠላትን የዩራኒየም ማበልፀጊያ ገደብ እንድታልፍ አድርጓል፡፡
ቴሄራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሚውል በተደጋጋሚ ብትናገርም፤ ትራምፕን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን መሪዎች ሀገሪቱ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ከመገንባት ውጪ ምንም ጥቅም በሌለው ደረጃ ዩራኒየምን ወደማበልጸግ ተመልሳለች ሲሉ ይከሳሉ፡፡
በሀገሪቱ ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የማዕቀብ እና ሌሎች ማስፋራሪያዎቻቸው እንዳሉ ሆነው ውዝግቡን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እና በአዲስ የኒዩክሌር ስምምነት መቋጨት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡
በዚህ የትራምፕ ሀሳብ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ አዲስ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፤ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች ግን ከቃል አልፎ ተግባርን የሚጠይቁ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡
“ሁኔታው ካለፈው ጊዜ የተለየ እና በጣም አስቸጋሪ ነው፤ የእርስ በእርስ መተማመንን ለመፍጠር ከዛኛው ወገን (ከአሜሪካ) ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ፤ ነገር ግን እስካሁን ከቆንጆ ቃላት ባለፈ በተግባር ያየነው ነገር የለም ይህ ብቻውን ደግሞ በቂ እንዳልሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኒዩክሌር መርሀ ገብሩ የተነሳ በቴሄራን ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የሀገሪቱን የዋጋ ግሽበት 50 በመቶ ሲያደርሰው የወጣቶች የስራ አጥነት ደግሞ ወደ 20 በመቶ አሻቅቧል፡፡
በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና የኢራን አጋሮች መዳከምን በተመለከተ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቡድኖቹን መዳከም አምነው፤ ሀማስ እና ሄዝቦላህ ተጠናክረው ዳግም እንደሚመለሱ አሳስበዋል፡፡
“ሀማስ እና ሄዝቦላህ ተጎድተዋል። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ከደረሰባቸው ጉዳት ተምረው እራሳቸውን እየገነቡ ነው፤ የሚታገሉለት ሀሳብ ጠንካራ እና የማይሞት በመሆኑ ዳግም ያንሰራራሉ የትግል አላማቸውም ሁል ጊዜም የሚኖር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።ኀ