በሺዎች የሚቆጠሩ ለቶተንሃም ደጋፊዎች የተዘጋጁ ትኬቶች አልተሸጡም ተባለ
የአርሰናል ደጋፊዎችም ያልተሸጡ ትኬቶችን ገዝተው የከተማ ተቀናቃኛቸው ማንቸስተር ሲቲን እንዲያሸንፍ ድጋፍ እንዲሰጡ እየተጠየቁ ነው
አሰልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ “የደርቢ ፉክክርን በሚገባ ባውቅም የትኛውንም ክለቡ እንዲሸነፍ የሚያስብ ደጋፊ ልረዳው አልችልም” ብለዋል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2023/24 ሻምፒዮንን ለመወሰን ትልቅ ድርሻ ያለው ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4 ስአት ላይ ይደረጋል።
የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም በሜዳው ለአራተኛ ተከታታይ አመት የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየተፎካከረ ያለውን ማንቸስተር ሲቲ ያስተናግዳል።
የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን ይህን ተስተካካይ ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉን መሪ አርሰናል በሁለት ነጥብ በመብለጥ ለሻምፒዮንነት የመጨረሻውን ጨዋታ ይጠባበቃል።
ቶተንሃም ካሸነፈ ወይም አቻ ከተለያዩ ደግሞ የከተማ ተቀናቃኛቸው አርሰናል ዋንጫውን ለማንሳት የእሁዱን ተጠባቂ ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ ይቀረዋል።
በዚህም ምክንያት የዛሬ ምሽቱን ፍልሚያ የቶተንሃም ደጋፊዎች በስታዲየም የመመልከት ፍላጎት እንደሌላቸው የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።
የእንግሊዙ ዘ ሰን ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ ለስፐርስ ደጋፊዎች የተዘጋጁ በሺዎች የሚቆጠሩ ትኬቶች እስካሁን አልተሸጡም ብሏል።
የክለቡ ደጋፊዎችም በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የምሽቱ ጨዋታ በሲቲ አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ፍላጎታቸው መሆኑን እየገለጹ ነው ይላል ዘገባው።
ትኬት የተሸጠባቸውን እና ክፍት የሆኑ ወንበሮችን የሚያሳይ ምስል በኤክስ (ትዊተር) ላይ ከተጋራ በኋላም በርካቶች የድጋፍና የነቀፌታ አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛሉ።
መድፈኞቹ በሲቲ ማሸነፍ የዋንጫ ግስጋሴያቸው እንዲገታ ክለባቸው መስዋዕት ቢሆን ግድ የማይሰጣቸው እንዳሉ ሁሉ “እብደት ነው፤ ክለቡ በሜዳው እንዲሸነፍ ስታዲየም ባዶ የሚያደርግ ደጋፊ አይተን አናውቅም” የሚሉና ሌሎች ትችቶችን የሰነዘሩ ደጋፊዎችም ታይተዋል።
የአርሰናል ደጋፊዎች በበኩላቸው እየተናነቃቸውም ቢሆን ዛሬ ደርቢያቸው እንዲያሸንፍ ወደ ቶተንሃም ስታዲየም ለመግባት ትኬቶችን እንደሚገዙ እየገለጹ ነው።
ምንም እንኳን በርካታ የቶተንሃም ደጋፊዎች የምሽቱን ጨዋታ ሲቲ እንዲያሸንፍ እንደሚፈልጉ እየገለጹ ቢሆንም አሰልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ ግን ለማሸነፍ እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።
“የደርቢ ስሜትን በሴልቲክና ሬንጀርስ አውቀዋለሁ” የሚሉት አሰልጣኙ፥ “ይሁን እንጂ የትኛውንም ክለቡ እንዲሸነፍ የሚፈልግ ሰው ልረዳው አልችልም፤ ይሄ ስፖርታዊ ባህሪ አይደለም” ብለዋል
አውስትራሊያዊው አሰልጣኝ ትክክለኛው ስኬት በዋንጫ መታጀብ ያለበት መሆኑን በመጥቀስም ዛሬ ወደሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ብቻ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ስፐርስ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ የዛሬውንና ቀጣይ ጨዋታውን ማሸነፍ ብሎም የአስቶንቪላን ነጥብ መጣል ይጠብቃል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን እሁድ በተመሳሳይ ስአት በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ሲያገኝ አርሰናል በኤምሬትስ ኤቨርተንን ያስተናግዳል፤ ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ዌስትሃምን ይገጥማል።