የጀርመኑ ቮልስዋገን በዓመቱ በርካታ መኪኖችን የሸጠ 2ኛው ግዙፍ የዓለማችን ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ነው ተብሏል
ግዙፉ የጃፓን መኪና አምራች ኩባንያ ቶዮታ በመኪና ሽያጭ የሚቀድመው አልተገኘም ተባለ፡፡
ቶዮታ በ2021 የዓለማችን ቀዳሚው ተሽከርካሪ ሻጭ ኩባንያ ነው ተብሏል፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት የዓለም አቀፉ ኩባንያዎች ዓመታዊ የተሽከርካሪ ሽያጭ ሪፖርት ይፋ ሆኗል፡፡
በሪፖርቱ መሰረት የጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያ 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማምረት ቀዳሚው ድርጅት ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የዓለማችንን የተሽከርካሪ አምራችነት ደረጃን ተቆጣጥሯል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 ዓመት 10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተሸከርካሪዎችን በማምረት የዓለማችን ቀዳሚው ኩባያ የነበረው የጀርመኑ ቮልስዋገን ኩባንያ ደረጃውን በቶዮታ ተነጥቋል፡፡
ኩባንያው በተጠናቀቀው 2021 ዓመት 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማምረት ለዓለም አቀፍ ገበያዎች ማቅረቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካው ጀነራል ሞተርስ አውቶሞቲቭ ኩባንያ ደግሞ በዚህ ተመሳሳይ ዓመት 7 ሚሊዮን ገደማ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ሶስተኛው የዓለማችን ኩባንያ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የቶዮታ ኩባንያ ዓመታዊ የሽያጭ መጠን በ10 በመቶ የጨመረ ሲሆን የቀሪዎቹ ኩባንያዎች ግን የሽያጭ መጠኑ መቀነሱ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ እና አውሮፓ ኩባንያዎች ለዓመታዊ የሽያጭ መጠናቸው መቀነስ የኮሮና ቫይረስ በእስያ ያስከተለው ጉዳት በአውሮፓ እና አሜሪካ ካደረሰው ጉዳት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑ ዋነኛው ምክንያት እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡