የጃፓን ተመራማሪዎች በ3D ቴክኖሎጂ ስጋ ፈጥረናል እያሉ ነው
የኦሳካ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለቢፍ ስጋ ሲባል ከዚህ በኋላ ከብት ማረድ አይጠበቅብንም ብለዋል
በባዮ ፕሪንቲንግ ቴክኖሎጂ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ ስጋው ከላም የተወሰደ የህዋስ ፋይበር በመጠቀም ነው የተሰራው
የጃፓን ኦሳካ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ስጋን በ3D ቴክኖሎጂ አማካኝነት ማምረት የሚቻልበት መንገድ አግኝተናል እያሉ ነው።
“አንድ ቀን ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ይውላል” ያሉት ፈጠራው ለቢፍ የሚሆን የተቆረጡ ስጋዎችን ዘላቂነት ባለው መልኩ በማምረት ዋናውን ከብቶችን በማረድ የሚገኘውን ይተካል ብለው እንደሚያምኑ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ተመራማሪዎቹ ስጋውን ለመስራት የከብት የህዋስ ግንድ (stem cells) መጠቀማቸውን የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፤ በዚህም ለቢፍ ስጋ የሚሆነውን ህዋስ (cell) ከለዩ በኋላ የደም ቧንቧ፣ ጡንቻ እና ስቦችን አንድ ላይ አደራጅተዋል፤ በመቀጠልም ሕብረ ሕዋሳቱን ቅርጽ በማስያዝ “3D ባዮ ፕሪንቲንግ” የተባለ ቴክኒክ በመጠቀም ስጋውን መስራታቸው ታውቋል።
በኦሳካ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድኑ አባል የሆኑት ሚቺያ ማትሱሳኪ ጥናቱን አስመለክቶ በሰጡት መግለጫ፤ “ይህንን ቴክኖሎጂ በማሻሻል በስጋ ውስጥ የተመጣጠነ ስብ እና ጡንቻ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።
በቅርቡ ስጋ ተመጋቢዎች በ3D ቴክኖሎጂ አማካኝነት የተመረተ ስጋ አዘው እንደሚመገቡ እምነት እንዳላቸውም ነው ተመራማሪው የተናገሩት።
በ3D ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚመረተው ስጋ ተመጋቢዎች የሚፈልጉትን ጣእም እንዲያገኙ እንዲሁም ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚስችላቸው እንደሆነም አስታውቀዋል።
ስጋ በ3D ቴክኖሎጂ አማካኝነት ለማምረት ሙከራ ሲደረግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ያለው ዘገባው፤ ከዚህ ቀደምም በእስራኤል የማምረት ሙከራ ተደርጎ ነበር።
የእስራኤል ትቺየን ዩኒቨርሲቲ የባዮ ሜዲካል እንጂነሪንግ ክፍል ከአሌፍ ፋርም ጋር በጋራ በመሆን በሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ትክክለኛ የላም ሴል ተጠቅመው በ3D ቴክኖሎጂ ስጋ ሰርተው ነበር።