ለልማቱ የሚሆን 32 ነጥብ 5 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም ተገልጿል
ጃፓን በኢትዮጵያ የመምህራን ልማትን ልትደግፍ ነው
ጃፓን ለተለያዩ ሰብዓዊ ተግባራት የሚውል 32 ነጥብ 5 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍን ለኢትዮጵያ ልታደርግ ነው፡፡
ድጋፉ በዋናነት ከትምህርት ስርዓቱ ጋር ተካተው ለሚተገበሩ የሰላም ግንባታ እና የመምህራን ልማት ተግባራት የሚውል ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ካደረገችው የ11 ነጥብ 1 ሚሊዬን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ በሶስት እጥፍ እንደሚበልጥም ነው በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ማትስናጋ ዳይስኬ የተናገሩት፡፡
በተቀረው የአፍሪካ ክፍል ያለውን የመምህራን ልማትን ለመደገፍ የሚያስችላትን የ14 ሚሊዬን ብር ስምምነትም ዛሬ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አድርጋለች፡፡
ስምምነቱ በዋናነት ሰላምንና ግጭት ማስቀረትን ታሳቢ አድርጎ በዩኔስኮ የአፍሪካ አቅም ግንባታ ተቋም (IICBA) በኩል የሚፈጸም ሲሆን አፍሪካ ህብረት ከያዘው የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን የመፍጠር ራዕይ ጋር ተጣጥሞ ይተገበራል ተብሏል፡፡
አምባሳደር ማትስናጋ ዳይስኬ እና የIICBA ዋና ዳይሬክተር ዩሚኮ ዮኮዜኪ (ዶ/ር) ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡
ድጋፉ ትውልድ የሚቀርጹትን የአህጉሪቱን መምህራን ታሳቢ አድርጎ የሚፈጸም ነው ያሉት አምባሳደር ማትስናጋ መምህራን ሰላምን የማቀንቀንና እሴቶቹን የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባቸው በፊርማ ስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ባለፉት 3 ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ እና በሳህል አካባቢ በተተገበሩ ተመሳሳይ የሰላም ትምህርት ፕሮጄክቶች አበረታች ውጤት መገኘቱንም ነው የገለጹት፡፡
ዩሚኮ ዮኮዜኪ በበኩላቸው የሰላም ጉዳይ በትምህርት ውስጥ ሊካተት ካልቻለ የሰላም ግንባታ ጥረቱ ስኬታማነት ተጠየቅ ውስጥ እንደሚወድቅና ዘላቂነት እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡
የሰላም ጽንሰ ሃሳቦች እና እሴቶች በወጣቶች አዕምሮ ውስጥ ሊዳብሩ እንደሚገባ የተናገሩም ሲሆን ይህን በማሳደግ ረገድ የመምህራን ሚና የማይተካ እንደሆነና የፕሮጄክቱ አስፈላጊነት ይኸው ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡
ከአሁን ቀደም በነበሩ ተሞክሮዎች የተገኙ ልምዶችን በመቀመር ወደ ተቀረው የአህጉሪቱ ክፍል ለማዳረስና ፕሮጄክቱን ለመተግበር እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡