በፈረንጆቹ 2021 በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከናወኑ አበይት ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ቀዳሚዎቹ የትኞቹ ናቸው?
የፈረንጆቹ 2021 ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ብቻ ይቀረዋል፡፡በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረውና አንድ አመት ያለፈው ጦርነት በጠቅላላ ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረ ቢገለጽም ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ ሁነቶች ለማከናዋን መንግስት ጥረት ማድረጉን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡በዚህ አመት በኢትዮጵያ ውስጥ የተከናውኑ አበይት ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
- አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎአ ንግድ ትስስር ተጠቃሚነት ሰረዘች
- ኢትዮጵያ ከአሜሪካው አጎአ እንድትወጣ “የሚጎተጉቱ”ት እነማን ናቸው?
- ኢትዮጵያ ድርሻ ባላት በርበራ ወደብ መርከብ ማሰማራት ጀመረች
የበርበራ ወደብ ስራ መጀመር
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የውጭ ንግድ ልውውጥ የምታደርገው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑ ይታወቃል፡፡ አማራጭ ወደቦችን ለማግኘት አትዮጵያ የተለያዩ ጥረቶች ስታደርግ ቆይታለች፡፡በርበራ ወደብ አንዱ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የሶማሌላንዱን በርበራ ፖርትን መጠቀም የጀመረው በዚህ አመት ነው፡፡
በበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ወደ በርበራ ወደብ መርከብ ማሰማሯቷን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎ አስታውቆ ነበር፡፡ ጊቤ የተሰኘችው የኢጥዮጵያ መርከበር ወደቡ ላይ እቃ በማራገፍ የመጀመሪያዋ ሆና ነበር፡፡
“ድርጅታችን ወደ በርበራ ወደብ መደበኛ አገልግሎት መስጠት የጀመርንበት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጉዞ ጊቤ በተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ማሳካት” መቻሉ እንዳስደሰተው ድርጅቱ በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የበርበራ ወደብ በዲፒ ወርልድ የ51%፣ በሶማሊላንድ የ30% እና በኢትዮጵያ የ19% ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡
የወደቡ ተርሚናል ኮሪደር የመጀመሪያ ዙር የማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቲነሮችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በአመት አንድ ሚሊዬን ኮንትነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በዱባይ ኤክስፖ2020
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች(ዩኤኢ) እየተካሄደ ያለው ኤክስፖ2020፤ከ192 ሀገራትና 25 ሚሊዮን ተሳታፊዎች ያስተናግዳል የተባለ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ክስተት ነው፡፡ኤክሰፖው ባለፈው መስከረም ወር የተጀመረ ሲሆን ለስድስት ተከታታይ ወራት ይቆያል፡፡
በዱባይ ኤክስፖ2020፣ለኢትዮጵያ በተዘጋጀው አልፍኝ፤ የኢትዮጵያ ልኡክ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጭችን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡በኤክስፖው፤ኢትዮጵያን የሚወክሉ ሙዚቃዎችና እና ባህሎች እንደሚቀርቡ መንግስት አስታውቆ ነበር፡፡
በኤክስፖው፣ሉሲ ወይንም ድንቅነሸ ቀደም ሲል ወደ ዱባይ መወሰዷም ይታወቃል፡፡ ዱባይ ኤክስፖ2020፣በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ዝግጅቱ 10 አመታትን እንደፈጀ ተገልጿል፡፡
ለውጭ ኩባንያ የተሰጠ የቴሌኮም ፍቃድ
የኢትዮጵያ መንግሰት ሊተግብር ካሰበው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከል የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር አንዱ ነው፡፡ መንግስት ወደ ግል እንዲዞሩ ካሰባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል የቴለኮም ዘርፉ አንዱ ነው፡፡
በቴሌኮም ዘርፍ በጨረታው ተጋብዘው ከነበሩት ከፍተኛ ገንዘብ ያስመዘገበው ግሎባል ፓርትነርሽብ ፎረ ኢትዮጵያ ጨረታውን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የሙዓለ ነዋይ ፍሰት ዕቅድ ላቀረበው ለግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ፣ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አዲስ ሀገር አቀፍ የቴሌኮም ፈቃድ እንዲሰጥ በአንድ ድምፅ አጽድቋል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ታሪካዊ ውሳኔ” መወሰኑን መግለጹ ይታወሳል።
በአጠቃላይ ከ 8 ቢሊዮን ዶላር በሚበልጥ የሙዓለ ነዋይ ፍሰት፣ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የሙዓለ ነዋይ ፍሰቶች የአሁኑ ኩባንያ ብልጫ እንዳላውም ተገልጿል፡፡
የቮዳፎን ግሩፕ አባል በሆነው ሳፋሪኮም የሚመራው ይህ ጥምረት በፈረንጆቹ ከ2022 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ጀምሮ በአስር ዓመት ጊዜ ለመንቀሳቀስ የሚያችለው ከ8.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ ፤ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለመጀመር አቅደዋል፡፡
ኩባንያው በፈረንጆቹ አዲስ አመት(2022) ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ከአሜሪካው የገበያ ትሰስር(አጎአ)መሰረዝ
የኢትዮጵያ መንግስት፤አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከተውን ግጭት የምታይበትን መንገድ ባለመቀበሉ ምክንያት ሁለቱ ሀገራት አለመግባባት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን ሀገራት ሁሉንም አይነት ጫና እያሳደሩበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲከስ ቆይቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳን ጆ ባይደን፣ኢትዮጵያ ከአሜሪካው ከቀረጥና ኮታ ነጻ ከሆነው የንግድ ችሮታ(አጎኣ) ያላት ተጠቃሚነት እንዲያበቃ ለኮንግረስ መጻፋቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከንግድ ችሮታው የሚያስወጣ ውሳኔ የወሰኑት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘና መሆኑን ኋይት ሃውስ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የአሜሪካ ባለስልጣናት መካከል ውይይት ቢካሄድም፤አሜሪካ እርምጃውን ከመውድ አልተቆጠበችም፡፡ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ከአጎኣ የገበያ ትስስር የሚሰረዝ ፊርማቸውን በቅርቡ አኑረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ“በእኛ እምነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአጎአ ተተቃሚ መሆን የምንችለው አሁን ነው” ብለው ነበር።
አቶ ማሞ በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት የተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የአጎዋ አባልነት የሚያጠናክሩ ናቸው ብለውም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከንግድ ትስስሩ እንድትወጣ የሚጎተጉቱ አካላት መኖራቸውን አቶ ማሞ ገልጸው ነበር፡፡
የአሜሪካ መንግስትን ወሳኔ የተቃወመችው ኢትዮጵያ፤ውሳኔው እንዲቀለበስ መጠየቋ ይታወሳል፡፡ ነገረግን እስካሁን በአሜሪካ በኩል የአቋም ለውጥ አልተሰማም፡፡