ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዳግም ከተመረጡ በኋላ ኢኮኖሚ ዋነኛ ፈተና ሆኖባቸዋል ተብሏል
በፈረንሳይ በተካሄደ የሰራተኞች አመጽ ትምህርት ቤቶች እና ትራንስፖርት ተስተጓጎለ።
ከስምንት ወራት በፊት የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋን እንዲያሻቅብ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የጦርነቱ ጉዳት ለዓለም ሀገራት ቢሆንም በአውሮፓዊያን ላይ ግን በተለይ የነዳጅ ዕጥረት ብዙ ጉዳቶችን እድርሷል።
በታሪክ ከፍተኛውን የዋጋ ግሽበት እያስተናገዱ ያሉት አውሮፓዊያን ዜጎች መንግስታቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የአውሮፓ ሁለተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ፈረንሳይ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የስራ አድማውን በተለይም የባቡር ጣቢያ እና መምህራን በዛሬው ዕለት በማድረጋቸው በፈረንሳይ ዋናዋና ከተሞች ትምህርት እና ትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሉ ተገልጿል።
በሰራተኞች ማህበራት የተጠራው ይህ የስራ ማቆም አድማ ላይ በመላው ፈረንሳይ ባሉ ከተሞች ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል ተብሏል።
ሰራተኞቹ የሀገራቸው መንግስት ለኑሮ ውድነቱ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም እና የደመወዝ ጭማሪ ይደረግልን ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል።
በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚመራው የፈረንሳይ መንግስት በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የማሻሻያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ ዳግም ከተመረጡ በኋላ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት እና ምርት እጥረት ትኩረት አልሰጡም የሚሉ ታቃውሞዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።