ቡርኪናዊያን የፈረንሳይን ኤምባሲ ያቃጠሉት ከስልጣን የተወገዱት ኮለኔል ዳሚባን ደብቃለች በሚል ነው
የቡርኪናፋሶ ዜጎች በኡጋዲጉ የፈረንሳይ ኤምባሲን ማቃጠላቸው ተገለጸ።
በምዕራብ አፍሪካዋ ቡርከናፋሶ የሀገሪቱ ጦር ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በምርጫ ስልጣን ይዘው በነበሩት ፕሬዝዳንት ካቦሬ ላይ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡
በኮለኔል ሳንዶጎ ዳሚባ የተመራው ይህ መፈንቅለ መንግስት አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው የሀጊቱ ልዩ ሀይል በሚባል ጦር ከትናንት በስቲያ ዳግም መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ የተፈጸሙት ሁለት መፈንቅለ መንግስቶች ዋነኛ ምክንያታቸው የሀገሪቱ መንግስት በጽንፈኛ ታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ማስቆም አልቻሉም በሚል ነው፡፡
ላለፉት 10 ወራት ስልጣን ላይ የነበሩት ኮለኔል ዳሚባ ስልጣናቸውን በመፈንቅለ መንግስት ቢነጠቁም እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ተገልጿል፡፡
የኮለኔል ዳሚባ መሰወር ያስቆጣቸው ቡርኪናዊያን ፈረንሳይ እንደደበቀችው የጠረጠሩ ሲሆን በኡጋዲጉ የሚገኝ የፈረንሳይ ኢምባሲን አቃጥለዋል፡፡
ኮለኔል ዳሚባን በቡርኪናፋሶ የሚገኘው የፈረንሳይ ጦር ሳይደብቀው እንዳልቀረ የጠረጠሩ ቡርኪናዊያን ከኡጋዲጉ በተጨማሪ ቦቦ ዲየላሶ በተሰኘች ከተማ ያለውን የፈረንሳይ ኢንስቲትዩት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል አርቲ ዘግቧል፡፡
ከትናንት በስቲያ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ልዩ ሀይል ሌተናል ኮለኔል ጂያን ካብሬ ከሰሞኑ ከስልጣን በሀይል የተወገዱት ኮለኔል ዳሚባ በፈረንሳይ ጦር እርዳታ መልሰው ስልጣን ለመቆጣጠር እየተዘጋጁ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በሀገራቸው ባለው የፈረንሳይ ጦር የተበሳጩት ቡርኪናዊያን ደግሞ የፈረንሳይ በሆኑ ተቋማት እና ንብረቶች ላይ ጉዳቶችን በማድረስ ላይ እንደሆኑ ዘገባው አክሏል፡፡
የፈረንሳይ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በቡርኪናዊያን እየተነሱ ባሉ ቅሬታዎች ዙሪያ በሰጠው ምላሽ ከስልጣን የተወገዱት ኮለኔል ዳሚባን የፈረንሳይ ጦር አልደበቀም፣ ወደ ስልጣን እንዲመለሱም ድጋፍ አላደረገም ብሏል፡፡