የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት፤ “ማናኛውም ሀገር በዩክሬን ጦርነት ላይ ገለልተኛ ሆኖ መቆየት አይችልም” አሉ
ማክሮን፡ ሞስኮ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ያለው “ወረራ” ፈረንሳይ አትቀበልም ብለዋል
ፕሬዝዳንት ማክሮን ፤ በራስ ወዳድነት ዝምታን የመረጡት አካላት በዬክሬን ጉዳይ “ድምጻቸው እንዲያሰሙ” ጠይቀዋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ “ማናኛውም ሀገር በዩክሬን ጦርነት ላይ ገለልተኛ ሆኖ መቆየት አይችልም” አሉ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 77ኛው ተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ለዓለም መሪዎች ባደረጉት ንግግር ላይ ነው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ፍትሃዊ እንዳልሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ የሚደመጡት የፈረንሳዩ መሪ፤ ሞስኮ በኪቭ ላይ እያከሄደች ያለው ዘመቻ ከ”ኢምፔሪያሊዝም ዘመን” ጋር አመሳስለውታል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን፤ "ከየካቲት 24 ጀምሮ ያየነው ነገር ወደ ኢምፔሪያሊዝም እና የቅኝ ግዛት ዘመን እንደመመለስ ነው፤ ፈረንሳይ ይህን አልተቀበለችም እናም ለሰላም በጽናት ትሰራለች" ሲሉም አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ በራስ ወዳድነት ምክንያት ዝምታን የመረጡት አልያም በድብቅ ተባባሪ የሆኑት አካላት ድምጻቸውን ማሰማት ካልጀመሩ የዓለም ሰላም እውን ማድረጉ ቀላል እንደማይሆንም አስጠንቅቀዋል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፑቲን በዩክሬን ጉዳይ “ታሪካዊ ስህተት ሰርቷል“ ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ማክሮን በቅርቡ ለጋዜጦች በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ጦርነቱ ቆሞ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ የአስታራቂነት ሚና እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"እኔ እንደማስበው እና እንደነገርኩት ፑቲን ለህዝቡ፣ለታሪክ እንዲሁም ለራሱ ታሪካዊ እና መሰረታዊ ስህተት እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡