ትራምፕ በ40 ቀናት ውስጥ 79 የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ በመፈረም ክብረወሰን ሰበሩ
ባይደን በአንድ አመት የፈረሙትን ትዕዛዝ የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት በ40 ቀናት መፈረማቸው በመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ፈጣን ለውጥ ለማሳየት መፈለጋቸውን ያሳያል ተብሏል

16ቱ የትራምፕ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች ተቃውሞ ተነስቶባቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ነው
ሪፐብሊካኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ በመፈረም ክብረወሰን ያዙ።
ትራምፕ በ40 ቀናት ውስጥ 79 የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ በመፈረም ከ1937 ወዲህ በርካታ ትዕዛዝ የፈረሙ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዋል ብሏል የአሜሪካ የፌደራል መዛግብት በድረገጹ ባወጣው መረጃ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው (2017-2021) የመጀመሪያ 40 ቀናት የፈረሙት 17 የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ብቻ ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጅ ባይደንም በስልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ አመት የፈረሙት ትራምፕ በ40 ቀናት ከፈረሙት ጋር እኩል ነው ተብሏል።
የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞቹ መበራከት ትራምፕ በመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ፈጣን ለውጥ ለማምጣት የያዙት እቅድን እንደሚያመላክት የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል።
ፕሬዝዳንቱ ከፈረሟቸው ትዕዛዞች ውስጥ ሲሶ የሚሆኑት በባይደን አስተዳደር ውድቅ የተፈረሙትን ውድቅ የሚያደርጉና የሚያሻሽሉ ናቸው።
ከ79ኙ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች ውስጥ 16ቱ ተቃውሞ ተነስቶባቸው በፍርድቤት እየታዩ ይገኛሉ።
ኢኮኖሚ እና ንግድ
ትራምፕ ከፈረሟቸው የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ናቸው። በቻይና፣ ሜክሲኮ እኛ ካናዳ የሚጣሉ ታሪፎችን የተመለከቱ እና በርካታ የታዳሽ ሃይል ፕሮጀክቶችን የሰረዙባቸውን ትዕዛዞች ፈርመዋል። የኒውዮርኩ ቢሊየነር ወደ ታዳሽ ሃይል ሽግግሩ "ቅጥፈት" ነው በሚል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና የነፋስ ሃይል ማመንጫዎች ፕሮጀክቶችን የሚገድቡ ትዕዛዞች ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውም ይታወሳል።
የጾታና ብዝሃነት ጉዳዮች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁለት ጾታዎች (ወንድ እና ሴት) ብቻ እውቅና የሚሰጥ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል። በአሜሪካ ጦር ውስጥ ጾታ የቀየሩ ወታደሮች እንዳይካተቱም አግደዋል።
እድሜያቸው ከ19 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ጾታቸውን የመቀየር ሂደት እንዳይጀምሩና በትምህርት ተቋማትና አለማቀፍ ውድድሮች ላይም ጾታቸውን የቀየሩ ወንዶች በሴቶች ስፖርታዊ ፉክክሮች እንዳይሳተፉ ማገዳቸው ይታወሳል።
ትራምፕ የ"ብዝሃነት፣ እኩልነት እና አካታችነት" ፖሊሲን የሚቃረኑ 14 የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ከስደተኞች ጋር የተያያዙ
ከ79ኙ የትራምፕ ስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች 16ቱ ከስደተኛ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው። ለስደተኞች ድጋፍ የሚያደርግተቋማት ገንዘብ
ትራምፕ በአሜሪካ ህገመንግት 14ኛ ማሻሻያ የጸደቀውን መብት ሽረው በአሜሪካ መሬት የተወለደ ሁሉ የሀገሪቱ ዜጋ አይሆንም የሚል ትዕዛዝ ፈርመዋል። በርካታ የፌደራል ዳኞች ይህ ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዳይሆን ያገዱት ሲሆን ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ፍርድቤት ሊያመራ እንደሚችል ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንግሊዝኛን ብቸኛው የፌደራል ቋንቋ የሚያደርግ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
የመንግስት ስራ ውጤታማነት
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ ለሚሰራው በምዕጻሩ "ዶጅ" ለተሰኘ ተቋም ቢሊየነሩ ኤለን መስክን ሾመው ስድስት ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ትዕዛዞችን ፈርመዋል። የመንግስት ተቋማት እና ሰራተኞችን እንዲሁም አላስፈላጊ ቢሮክራሲዎችን ለመቅረፍ ያስችላሉ ያሏቸውን እርምጃዎችም እየወሰዱ ነው።
ጤና እና ቴክኖሎጂ
በጤናው ዘርፍ ከተላለፉ 13 የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዞች ውስጥ አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት ማስወጣት፣ የባይደን አስተዳደርን የጽንስ ማስወረድ ፈቃድ መከልከል እና ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር የተያያዙት ይገኙበታል።
የኤለን መስክ ወዳጅ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ 10 ትዕዛዞችንም ፈርመዋል። ከነዚህ ውስጥ ሶስቱ ከአሪፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ጋር የሚያያዙ ሲሆኑ፥ ሁለቱ የምዕናብ ግብይት (ክሪፕቶከረንሲ)ን ይመለከታሉ።