ትራምፕ ሰርዘውታል የተባለው ትዕዛዝ "ኤንኤስኤም 20" ምንድን ነው?
ትዕዛዙ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ቦምቦች በጋዛ ንጹሃንን እየጨረሱ ነው የሚል ተቃውሞ ከተነሳ በኋላ የፈረሙት ነው

ትራምፕ ይህን ትዕዛዝ መሻራቸው እስራኤልን ጨምሮ የአሜሪካ አጋሮች ከዋሽንግተን እንዳሻቸው የጦር መሳሪያ እንዲገዙና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገሪቱ ለውጭ ሀገራት የምትሸጣቸው የጦር መሳሪያዎች አለማቀፍ ህግን እንዳልጣሱ ለማረጋገጥ ሪፖርት እንዲቀርብ የሚጠይቀውን ትዕዛዝ መሻራቸው ተነገረ።
"ናሽናል ሴኩሪቲ ሜሞራንደም (ኤንኤስኤም - 20)" የሚል ስያሜ የተሰጠውን ትዕዛዝ የፈረሙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ነበሩ።
ባይደን ትዕዛዙን የፈረሙት የአሜሪካ ቦምቦች በጋዛ የፍልስጤማውያን ንጹሃንን ህይወት እየቀጠፉ ነው የሚሉ ተቃውሞዎች መበርከታቸውን ተከትሎ እንደነበር ሬውተርስ አስታውሷል።
"ኤንኤስኤም - 20" የአሜሪካ መንግስት እስራኤልን ጨምሮ ለሌሎች አጋር ሀገራት የሚሸጡ የጦር መሳሪያዎች ለምን ጥቅም ሊውሉ እንደሚችሉ ለኮንግረንሱ ዝርዝር ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚጠይቅ ነው።
ገዥዎቹ ሀገራትም አለማቀፍ የጦርነት ህግን በጣሰ መልኩ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎችን ጥቅም ላይ እንደማያውሉና ጉዳት በሚደርስባቸው አካባቢዎችም አሜሪካ የሰብአዊ ድጋፍ እንድታደርግ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የጽሁፍ ማረጋገጫ እንዲሰጡ ይጠይቃል።
በግንቦር ወር 2024 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በጋዛ የአሜሪካን ቦምቦች ባልተገባ መንገድ እየተጠቀመች ነው በሚል በተለይ "ኤምኬ-84" የተሰኘው ቦምብ ወደ እስራኤል እንዳይገባ ማገዳቸው የሚታወስ ነው።
በባይደን አስተዳደር በእስራኤል ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ያነሱት ትራምፕ በቅርቡ ደግሞ "ኤንኤስኤም - 20" ትዕዛዝን መሰረዛቸውን ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የዋይትሃውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኬል ዋልዝ ትዕዛዙ መሰረዙ መሰረዙን ማሳወቃቸውንም ዘገባው አክሏል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የ"ኤንኤስኤም 20" መሰረዝ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ የትኛውንም የአለም ንጹህ ህዝብ እንዲጨርስ እንደመፍቀድ ይቆጠራል በሚል እየተቃወሙት ነው።
የአሜሪካን የጦር መሳሪያ ንግድ የሚከታተለው የኮንግረንስ ኮሚቴ አባሉና የሜሪላንዱ ሴናተር ክሪስ ቫን ሆልተንም ትዕዛዙን መሰረዝ "አሳፋሪ" ነው ብለዋል። ውሳኔው የአሜሪካን አለማቀፍ ተቀባይነት የሚጎዳ እና በመላው አለም የሰብአዊ መብቶች እንዲረገጡ በር የሚከፍት ነው ሲሉም አክለዋል።
"ኤንኤስኤም-20" ለሁሉም ከአሜሪካ የጦር መሳሪያ በሚገዙና በጦርነት ውስጥ ባሉ ሀገራት ተፈጻሚ የነበረ ሲሆን፥ የመሰረዙ ዋነኛ ምክንያት እስራኤል እንደሆነች ይታመናል።
ቴል አቪቭ በጋዛ ለ15 ወራት በፈጸመችው ድብደባ ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት ሲያልፍ የአሜሪካ ቦምቦች ድርሻ ትልቅ ነው፤ የባይደን አስተዳደርም ካደረገው መጠነኛ የቦምቦች እገዳ ውጪ "ኤንኤስኤም-20" ያስቆመው የጦር መሳሪያ ሽያጭ የለም።
የትራምፕ አስተዳደርም ከሰብአዊ መብት ይልቅ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ለሚገኘው ገቢ ቅድሚያ እንደሰጠ የሚያመላክተው ውሳኔ የሚጠበቅ መሆኑን የሚያነሱ ተንታኞች፥ የሀገሪቱ የጦር መሳሪያ ንግድ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል ብለዋል።