ትራምፕ እንግሊዝኛን የአሜሪካ ይፋዊ ቋንቋ የሚያደርግ ትዕዛዝ ፈረሙ
ውሳኔው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ያወጡትን የፌደራል ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማት እንግሊዝኛ በሚገባ ለማይናገሩ ሰዎች የቋንቋ እገዛ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ትዕዛዝ የሻረ ነው

በአሜሪካ ከ350 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን፥ ከ30 በላይ ግዛቶች እንግሊዝኛን የመንግስት ቋንቋ አድርገዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንግሊዝኛን የአሜሪካ ብቸኛው ይፋዊ ቋንቋ የሚያደርግ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈረሙ።
በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተላለፈው ውሳኔ "የጋራ ብሄራዊ እሴትና አንድነት" ለመፍጠር እንደሚያግዝ ዋይትሃውስ ገልጿል።
"እንግሊዝኛ ይፋዊ (የፌደራል መንግስት ስራ እና ሰነዶች) ቋንቋ መሆኑ ተግባቦትን ከማሳለጥ ባሻገር ሁሉን አካታች እና ውጤታማ ማህበረሰብ ለመፍጠርም ወሳኝ ድርሻ አለው" ነው የሚለው ትራምፕ የፈረሙት ትዕዛዝ።
"እንግሊዝኛ መናገር በኢኮኖሚ ረገድ የተዘጉ በሮችን ይከፍታል፤ ከዚህም ባለፈ አዳዲስ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ሰዎችን በብሄራዊ ጉዳዮች እና ባህሎች ላይ ተሳትፏቸውን በማሳደግ ለሀገራችን ማህበረሰብ እንዲጠቅሙ ያግዛል" ሲልም አክሏል።
የትራፕም ውሳኔ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን በፈረንጆቹ 2000 ያወጡትን የፌደራል ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማት እንግሊዝኛ በሚገባ ለማይናገሩ ሰዎች የቋንቋ እገዛ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ትዕዛዝ የሻረ ነው ተብሏል።
ውሳኔው ከእንግሊዝኛ ባሻገር በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት እና ሰነዶችን የሚሰጡ ተቋማት እንደየተልዕኳቸውና አገልግሎታቸው ማሻሻያ እንዲያደርጉ የሚፈቅድ መሆኑ ተገልጿል።
አሜሪካ ከትናንቱ የትራምፕ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ በፊት በፌደራል ደረጃ ይፋዊ ቋንቋ አልነበራትም። ለአስርት አመታት እንግሊዝኛን ብሄራዊ ቋንቋ ለማድረግ በኮንግረንሱ የተደረጉ ሙከራዎችም ሳይሳኩ መቅረታቸውን ዘ ጋርዲያን አስታውሷል።
ይሁን እንጂ ከ30 በላይ የአሜሪካ ግዛቶች እንግሊዝኛን ይፋዊ ቋንቋቸውን አድርገውታል።
በአሜሪካ ከ350 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን፥ ከ78 በመቶ በላይ የሀገሪቱ ነዋሪዎች እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ከእንግሊዝኛ በመቀጠል በሀገሪቱ ከፍተኛ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ስፓኒሽ ሲሆን፥ 13.4 በመቶ ተናጋሪ አለው። ከአሜሪካ ህዝብ 1 በመቶው ቻይንኛ ተናጋሪ መሆኑንም የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ መረጃዎች ያሳያሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ወር ቃለመሃላ እንደፈጸሙ የዋይትሃውስ ድረገጽን የስፔን ቋንቋ ክፍል ማዘጋታቸው ይታወሳል። ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸውም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው ባይደን ስልጣን ሲይዙ መከፈቱ አይዘነጋም።