ትራምፕ የየመኑን ሃውቲ በውጭ ሽብርተኛ ድርጅትነት ፈረጁ
ዋይትሃውስ ባወጣው መግለጫ ሃውቲዎች በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካውያንን ደህንነት አደጋ ላይ ጥለዋል ብሏል
የባይደን አስተዳደር በየካቲት 2021 የየመኑን ቡድን ከሽብርተኛነት ፍረጃው ማውጣቱ ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የየመኑን ሃውቲ ታጣቂ ቡድን በውጭ ሽብርተኛ ድርጅትነት ፈረጁ።
ፕሬዝዳንቱ ውሳኔውን ያሳለፉት ሃውቲዎች ከ2023 ጀምሮ በአሜሪካ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በማድረስ የሀገሪቱን ወታደሮች ደህንነት አደጋ ላይ ጥለዋል በሚል ነው።
ዋይትሃውስ ባወጣው መግለጫ የየመኑ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ንጹሃን አሜሪካውያን ላይም ስጋት መደቀኑን አመላክቷል።
የመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አጋሮች ብሎም የአለማቀፉን የባህር ላይ ንግድ ደህንነት እየፈተነ ነው የሚል ክስም ቀርቦበታል።
የዋይትሃውስ መግለጫ አሜሪካ ከቀጠናው አጋሮቿ ጋር በመሆን ሃውቲ በአሜሪካ ወታደሮችም ሆነ በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረስ በማይችልበት ደረጃ አቅሙን ለማሳጣት እንደምትሰራ ይገልጻል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሄራዊ ደህንነት እና ግምጃ ቤት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በ30 ቀናት ውስጥ የየመኑ ታጣቂ ቡድን በውጭ የሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲመዘገብ በ30 ቀናት ውስጥ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ሪፖርት እንዲያቀርብ ታዟል።
የአሜሪካ መንግስት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ)ም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለየመናውያን የሚላክ ድጋፍ በሃውቲዎች እጅ እንዳይገባ ግምገማ እንዲያደርግ በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
ሃውቲዎች መዲናዋን ሰንአ ጨምሮ አብዛኛውን ሰሜናዊ የሀገሪቱን ክፍል ተቆጣጥረዋል፤ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ህዝብም ቡድኑ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖር ነው።
ከየመን ህዝብ ከግማሽ በላዩ (19 ነጥብ 5 ሚሊየን) ሰብአዊ ድጋፍ የሚሻ መሆኑና ከአንድ ሶስተኛው በላይ የሀገሪቱ ክፍል በሃውቲዎች መያዙ በቡድኑ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች ለህዝቡ እንዳይተርፍ ያሰጋል።
ሃውቲዎች እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ለፍልስጤማውያን አጋርነታቸውን ለማሳየት በሚል በቴል አቪቭ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይም ከ100 በላይ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
የአሜሪካ መርከቦችም የሃውቲዎች የሚሳኤል ጥቃት ሰለባ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፥ አሜሪካ የቀይ ባህር ደህንነትን ለማስጠበቅ አጋሮችን አስተባብራ በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ድብደባ ፈጽማለች።
የአሜሪካም ሆነ የእስራኤል ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት በኢራን ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚታመነውን የየመን ታጣቂ ቡድን ወደ እስራኤል ሚሳኤል ከማስወንጨፍ አላስቆመውም።