ትዊተር የፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ትዊት ግጭት ቀስቃሽ ነው በሚል ከገጹ በማነሳቱ ነው የታገደው
የቀድሞው የዩኤስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናይጄሪያ ትዊተርን በማገዷመደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዝደንቷን በማገዱ ናይጄሪያ ትዊተርን አግዳለች ያሉት ሚስተር ትራምፕ ለዚህም ሀገሪቱን “እንኳን ደስ አለሽ” ብለዋል፡፡
ሌሎች ሀገራትም የናይጄሪያን ፈለግ በመከተል ትዊተርን ብቻ ሳይሆን ፌስቡክንም እንዲያግዱ ጠይቀዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዝደንት ባወጡት መግለጫ እነዚህን የማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያጣጥሉም ራሳቸው ክፉ ከሆኑ ፣ ጥሩውን እና መጥፎውን ሊለዩ እነርሱ ማናቸው ብለዋል፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ፌስቡክ እና ትዊተርን ማገድ እንደነበረባቸውም በቁጭት ገልጸዋል፡፡
ሚስተር ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ካስተላለፏቸው መልዕክቶች ጋር በተያያዘ በሁለቱም የማህበራዊ ሚዲያዎች የታገዱ ሲሆን ፣ ትዊተር እገዳው እስከመጨረሻ እንደሚጸና አስታውቋል፡፡ ፌስቡክ ደግሞ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያክል ከታገዱ በኋላ ፣ የፌስቡክም የኢኒስታግራምም አካውንታቸው እንደሚመለስላቸው ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የናይጄሪያ መንግስት ትዊትርን ማገዱን ተከትሎ በርከት ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች መንግስት ላይ ክስ መመስረታቸው ተሰምቷል።
ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ትዊተር የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የለጠፉትን ጽሁፍ “ግጭት ቀስቃሽ ነው” በሚል ከገጹ ማንሳቱ ይታወሳል።
የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገጹ የፕሬዝደንት ሙሃማዱ ቡሃሪን ትዊት ማጥፋቱን ተከትሉ ትዊተር በናይጄሪያ ውስጥ እንዳይሰራ አግደዋል።
መቀመጫቸውን ናይጀሪያ ያደረጉ የቴሌኮም ኩባንያዎችም በይፋ ትዊተር በሀገሪቱ ውስጥ እንዳይሰራ ማገዳቸው ነው የታወቀው።
የናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ህግም በተለያዩ ዘዴዎች ትዊተርን ሲጠቀም የተገኘ ሰው እስከ እስር የሚደርስ ቅጣት ይጠብቀዋል ሲል አስጠንቅቋል።
ጉዳዩ ያናደዳቸው በርከት ያሉ ናይጄሪያውያን የትዊተር እግዱ እንዲነሳ በቪ.ፒ.ኤን ተጠቅመው “#NigeriaTwitterBan እና #KeepitOn” በሚሉ ሀሽታጎች ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
ናይጄሪያውያኑ ከዚህም በዘለለ በትዊተር ላይ የተጣለው እግድ እንዲነሳ በሚል የናይጄሪያን መንግስት በቀጠናዊ ፍርድ ቤት ከሰዋል ነው የተባለው።
በሀገሪቱ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አና 176 ናይጄሪያውያን ናቸው የሀገሪቱን መንግስት በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የፍትህ ችሎት የከሰሱት።
በክሳቸውም የናይጄሪያ መንግስት በትዊተር ላይ የጣለውን እግድ በፍጥነት እንዲያነሳ መጠየቃቸው ታውቋል።