የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ ከሆስፒታል ወጡ
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በትራምፕ ላይ የተኮሰውን ግለሰብ ማንነት ይፋ አድርጓል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዛሬው እለት ከሀገሪቱ የደህንነትና ጸጥታ አመራሮች ስለግድያ ሙከራው ዝርዝር ሪፖርት ያደምጣሉ ተብሏል
የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ዶናልድ ትራምፕ ከሆስፒታል ወጡ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኒውጀርሲ ወደሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው ማቅናታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ ቀኝ ጆሯቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ፊታቸው በደም ተሸፍኖ ታይቷል።
ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራውን ያደረገው ግለሰብ በአሜሪካ ሚስጢራዊ የደህንነት ባለሙያዎች ወዲያውኑ መገደሉም ተገልጾ ነበር።
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ከጥቂት ስአት በፊት ባወጣው መግለጫ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ግለሰብ ቶማስ ማቲው የተባለ የ20 አመት ወጣት ነው ብሏል።
ማቲው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ሆኖ ወደ ትራምፕ እና የምርጫ ቅስቀሳው ታዳሚዎች ደጋግሞ ሲተኩስ ሚስጢራዊ ጠባቂዎቹ በፍጥነት ሊያስቆሙት ያለመቻላቸው ጉዳት አነጋጋሪ ሆኗል።
የፔንሲልቫኒያ ግዛት ፖሊስም ሚስጢራዊ የደህንነት ባለሙያዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ የተደረገበትን ስፍራ አስቀድመው መፈተሽ ነበረባቸው ሲል ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ አድርጓቸዋል።
ቶማስ ማቲው በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራውን ለምን እንደፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ይሁን እንጂ ማቲው የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የፔንሲልቫኒያ ነዋሪው ወጣት በፈጸመው ጥቃት አንድ የምርጫ ቅስቀሳው ታዳሚ ህይወቱ ማለፉና ሁለት ሰዎችም በጽኑ መቁሰላቸውን ተገልጿል።
በዳልዌር ሮሆቦት የባህር ዳርቻ በመዝናናት ላይ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዋሽንግተን የተመለሱ ሲሆን፥ ዛሬ ከደህንነትና የጸጥታ ሃላፊዎች ዝርዝር ሪፖርት ያደምጣሉ ተብሏል።
ታዋቂ የአሜሪካ ፖለቲከኞች የግድያ ሙከራውን በማውገዝ ላይ ሲሆኑ የሀገሪቱ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ባይደንም "ትራምፕ ደህና መሆኑ መልካም ነው፤ እንዲህ አይነት ህግወጥነት በአሜሪካ ቦታ የለውም" ሲሉ የግድያ ሙከራውን አውግዘዋል።