ቢሊየነሩ መስክ ለሪፐብሊካኑ እጩ ትራምፕ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተነገረ
ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያስፈልግ ገንዘብ የሚሰበስበው ፒኤሲ በፈረንጆቹ ሀምሌ 15 የለጋሾችን ስም ይፋ ያደርጋል

የባይደንን የስደተኞች እና የኤሌክትሪክ መኪና ፓሊሰን በይፋ ትችት የሚያቀርበው መስክ፣ ለትራምፕ ይፋዊ ድጋፍ አልሰጠም
ቢሊየነሩ መስክ ለሪፐብሊካኑ እጩ ትራምፕ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተነገረ።
በከሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ላይ ትችቱን አጠናክሮ የቀጠለው ቢሊየነሩ መስክ፣ ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጥ ለሚቀሰቅሰው ቡድን ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
መሰክ ድጋፉን ያደረገው አሜሪካ-ፒኤሲ ለተባለው ቡድን መሆኑን ሮይተርስ ብሉምበርግን ጠቅሶ ዘግቧል። ነገርግን መስክ ምን ያህል ድጋፍ እንዳደረገ ዘገባው አልጠቀሰም።
ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያስፈልግ ገንዘብ የሚሰበስበው ፒኤሲ በፈረንጆቹ ሀምሌ 15 የለጋሾችን ስም ይፋ ያደርጋል።
በቀጣይ ሳምንት ለህዳሩ ምርጫ በይፋ የሪፐብሊከን እጩ ሆነው የሚቀርቡት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ትራምፕ ባለፈው መጋቢት ከመስክ እና ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር ተገናኝተው ነበር።
ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊ መስክ "እኔ ለማንኛውም እጩ እንዳልሰጠሁ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ"ሲል በኤክስ ገጹ መልስ ሰጥቷል።
ባለፈው ግንቦት ወር መስክ ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነ መስክ በቤተመንግስት የአማካሪነት ሚና እንዲሰጠው ንግግር እየተደረገ ነው የሚሉ የሚዲያ ዘገባዎችን አስተባብሏል።
ሮይተርስ በዚህ ጉዳይ የአለም ቁጥር አንድ የሆነው ቢሊየነር መልስ እንዳልሰጠው ገልጿል።
የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቃል አቀባይ ጄምስ ሲንገር መስክ፣ ትራምፕ "መካከለኛ ገቢ ባላቸው አሜሪካዊውን ላይ ታክስ በ2500 ዶላር ከፍ አድርጎ የእሱን እንደሚቀንስለት" ያውቃል ብሏል።
"ጆ ባይደን እንደ መስክ ያሉ ሰዎችን ትተው፣ ህይወታቸው ሙሉ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ታግለዋል። በዚህ ምክንያት ነው የህዳሩን ምርጫ የሚያሸንፉት" ሲል ሲንገር አክሏል።
ሪፐብሊካን ፓርቲ ለመስክ ዋና የገቢ ምንጭ ለሆነው የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና ውቅና መቸራቸውን ተከትሎ መስክ በቅርብ አመታት የፓርቲው ደጋፊ ሆኗል።
ባለፈው ወር ትራምፕ የኤሌክትሪክ መኪና ኢንዱስትሪን የሚደግፈውን የባይደን አስተዳደር ኃላፊነት ወዲያውኑ እንደሚሰርዙት ተናግረው ነበር። ነገርግን ትራምፕ "የኤሌክትሪክ መኪና ዋና አድናቂ ነኝ። የኢሎን ደጋፊ ነኝ፤ በቴስላ የማይታመን ስራ እየሰራ ነው" ብለዋል።
መስክም ከትራምፕ ጋር ማውራቱን እና ትራምፕ የኤሌክትሪክ መኪና አድናቂ መሆናቸውን ተናግሯል።
የባይደንን የስደተኞች እና የኤሌክትሪክ መኪና ፓሊሰ እንዲሁም በእድሜያቸው ላይ በይፋ ትችት የሚያቀርበው መስክ፣ ለትራምፕ ይፋዊ ድጋፍ አልሰጠም።