ዶናልድ ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ማርክ ዙከርበግን እንደሚያሳስሩ ዛቱ
ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የምርጫ አጭበርባሪዎች የእጃቸውን ያገኛሉ ብለዋል
በ2020 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዙከርበርግ ለጆርጂያ ስቴት የለገሰው 2ሚሊየን ዶላር ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግን ጨምሮ “የምርጫ አጭበርባሪዎች” ያሏቸውን አካላት እንደሚያሳስሩ ዝተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ በተሰኝው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “እነኚህ አጭበርባሪዎች ሀፍረት አልፈጠረባቸውም በምርጫው የማሸንፍ ከሆነ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ወንጀላቸውን እናጋልጣለን” ብለዋል፡፡
“ማርክ ዙከርበርግ ማን እንደሆንክ እናውቃለን ያለፈውን ጥፋትህን እንዳትደግመው” በሚለው ጽሁፋቸው ከሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ባለፈ የምርጫ አጭበርባሪዎች የረጂም ጊዜ እስር ይጠብቃቸዋል ሲሉ ዝተዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ማርክ ዙከርበርግን በስም ከመጥራት ባለፈ “የምርጫ አጭበርባሪዎች” ያሏቸው አካላት እንማን እንደሆኑ በይፋ አልገለጹም፡፡
በ2023 ፎክስ ኒውስ የተባለው የአሜሪካ ሚዲያ በሰራው ዘገባ ዙከርበርግ ለጆርጂያ ስቴት ምርጫ ቦርድ ሁለት ሚሊየን ዶላር መስጠቱን አጋልጦ ነበር፡፡
ዘገባውን ተከትሎ ለምርጫ ቦርዱ ለምን ምክንያት እንደተሰጠ ያልታወቀው ገንዘብ ላይ ምርመራ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ይፋዊ የምርመራ ውጤት አልተገለጸም፡፡
ትራምፕ “ዴሞክራቶች የጥፋት አጋራቸውን በህግ ተጠያቂ ያደርጋሉ ብለን አንጠብቅም እስካሁን ድረስ ገንዘቡ በምን ምክንያት እንደተሰጠ እንኳን ሊያሳውቁን አልፈቀዱም” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በማህበራዊ ትስስር ጽሁፋቸው ስር ይህን የፎክስ ኒውስ ዘገባ ሊንክ ያስቀመጡት ትራምፕ በዘንድሮው ምርጫ ጣልቃ ሊገቡ ያሰቡ አካላት አይናችንን ገልጠን እየተከታተልናችሁ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት የጃንዋሪ ስድስቱ የካፒቶል ሂል አመጽ እንዲቀሰቀስ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጥሪ አድርገዋል በሚል ከማህበራዊ ትስስር ገጹ ሙሉ ለሙሉ ታግደው ነበር፤ እገዳው በ2023 ቢነሳላቸውም ትራምፕ ወደ ፌስቡክ ሳይመለሱ ትሩዝ የተባለ የራሳቸውን ማህበራዊ ትስስር ገጽ አቋቁመዋል፡፡
የ2024ቱን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጀመርያ ዙር ክርክርን ተከትሎ የትራምፕ የአሸናፊነት ግምት እያደገ ይገኛል፡፡