ትራምፕ የጋዛ ታጋቾች በፍጥነት ካልተለቀቁ በመካከለኛው ምስራቅ "ከባድ ችግር" ይፈጠራል አሉ
ትራምፕ "ይህን ግፍ የፈጸሙ በረጅሙ የአሜሪካ ታሪክ ማንም ከተመታው በላይ በከባዱ ይመታሉ"ብለዋል
ሀማስ ታጋቾቹን ለመልቀቅ ከመስማማቱ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ ጠይቋል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ የተያዙ ታጋቾች ከጥር 20ው በዓለ ሲመታቸው በፊት በፍጥነት ካልተለቀቁ በመካከለኛው ምስራቅ "ከባድ ችግር" ይፈጠራል ሲሉ በትናንትናው እለት ዝተዋል።
ሀማስ በ2023 በእስራኤል ላይ ከባድ ጥቃት በመፈጸም የእስራኤል-አሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎችን አግቶ መውሰዱን የእስራኤል መረጃ ያመለክታል።
በጋዛ ተይዘው ከሚገኙት 101 የውጭ እና የእስራኤል ዜጎች ውስጥ ግማሽ ገደማ የሚሆኑት በህይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።
ትራምፕ ከህዳሩ ምርጫው በኋላ ሰለታጋቾች እጣፋንታ በሰጡት ግልጽ አስተያየት "ታጋቾቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆኜ ቢሮ ከምገባበት ከጥር 20፣2025 በፊት ካልተለቀቁ በመካከለኛው ምስራቅ ከባድ ችግር ይፈጠራል፤ይህን ግፍ የፈጸሙትም ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል" ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም እንዳሉት "ይህን ግፍ የፈጸሙ በረጅሙ የአሜሪካ ታሪክ ማንም ከተመታው በላይ በከባዱ ይመታሉ።"
ሀማስ ታጋቾቹን ለመልቀቅ ከመስማማቱ በፊት ጦርነቱ እንዲቆም እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ ጠይቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀማስ እስከሚጠፋ እና የእስራኤል ስጋት እስከማይሆንበት ድረስ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ሀማስ በትናንትናው እለት በእስራኤል እና በሀማስ መካከል ለ14 ወራት በተካሄደው ጦርነት 33 ታጋቾች መገደላቸውን አስታውቋል። ሀማስ በጥቅምት 7፣2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት በማድረስ 1200 ሰዎችን ከገደለ በኋላ እስራኤል በጋዛ መጠነሰፊ ዘመቻ ከፍታለች።
በእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ44ሺ በላይ ማለፉን የጋዛ ባለስልጣናት ተናግረዋል። አብዛኛው የከተማዋ ክፍልም ፈራርሷል።