የግድያውን ሙከራ ያደረገው የ20 አመት አሜሪካዊ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ መሆኑ ተሰምቷል
በትላንትናው እለት በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያሉ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ትራምፕ ቀኝ ጆሯቸው ላይ ከደርሶባቸው ጉዳት ባለፈ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ጉዳት እንዳላጋጠማቸው ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ከጥቂት ስአት በፊት ባወጣው መግለጫ ትራምፕ ላይ የተኮሰው ግለሰብ ቶማስ ማቲው የተባለ የ20 አመት ወጣት ሲሆን በሪፐብሊካን ፓርቲ መራጭነት የተመዘገበ እንደነበርም ነው የተነገረው፡፡
አደጋውን ተከትሎ የተለያዩ የአለም ሀገራት መሪዎች የግድያ ሙከራውን ያወገዙ ሲሆን የእስያ ፣የመካከለኛው ምስራቅ ፣ የአውሮፓ እና የላቲን አሜሪካ መሪዎች ትራምፕ በቶሎ ያገግሙ ዘንድ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የ81 አመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እና የትራምፕ ተቀናቃኝ ጆ ባይደን አደጋውን ካወገዙ መሪዎች ቀዳሚው ሲሆኑ፤ በዴላዌር የባህር ዳርቻ የሳምንቱት የመጨረሻ ቀናት ለመሳለፍ የያዙትን እቅድ ሰርዘው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ተመልሰዋል፡፡
ከትራምፕ ጋር በስልክ የተነጋገሩት ፕሬዝዳነት ባይደን በቅርቡ በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ለመነጋገር እቅድ መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡
አዲሱ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር በሁኔታው እጅግ መደንገጣቸውን ሲገልጹ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው በፖለቲካ መሪዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው የፈሪዎች ድርጊት ነው ብለዋል፡፡
የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በቀጣዮቹ የአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳ እና የምርጫ ወቅት ጥላቻ እና አመጻ ይሸነፋሉ ብየ እጠብቃለሁ የግድያ ሙከራው በዴሞክራሲ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ትራምፕ ከደረሰባቸው ጥቃት በቶሎ እንዲያገግሙ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ደግሞ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዜለንሰኪ እና የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ናቸው፡፡
ዘለንስኪ መሰል ጥቃቶች ምክንያት አልባ እና በየትኛውም የአለም ክፍል ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ነው ያሉት፡፡
ከወደ ላቲን አሜሪካ የኮስታሪካ ፣ የአርጄንቲና ፣ ብራዚል ፣ ቺሊ እና ቦሎቪያ መሪዎች ድርጊቱን የኮነኑ ሲሆን፥ የብራዚሉ ፕሬዝዳነት ሉላ ዳሲልቫ "በሽብር እና በአምባገነንነት ሀሳብ ማስረጽ ያለፈበት ነው ፤ ድርጊቱን በዴሞክራሲ ጠባቂዎች በሙሉ ሊወገዝ የሚገባው ነው" ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከተደረገባቸው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተረፉት የቦሊቪያው ፕሬዝዳንት ሊዊስ አርሴ "ምንም እንኳን በፖለቲካ አመለካከት ብንለያይም አመጻ እና ጥቃት ከየትኛውም አቅጣጫ ቢመጣ ሊኮነን የሚገባው ነው" ብለዋል።
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ በበኩላቸው በወዳጄ ላይ በደረስው ጥቃት እጅግ አዝኛለሁ ያሉ ሲሆን፥ የጃፓኑ አቻቸው ፉሚዮ ኪሺዳ በፖለቲካ እና ዴሞክራሲ ውስጥ መሰል የፈሪ ምግባሮች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡
የካናዳ ፣ታይዋን ፣ ፊሊፒንስ ፣ አውስትራሊያ ፣ ኒውዝላንድ እና እስራኤል መሪዎች በተጨማሪ ድርጊቱን ካወገዙ እና ለዶናልድ ትራምፕ በፍጥነት ማገገም መልካም ምኞታችውን ከላኩ የሀገራት መሪዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የአረብ እና አፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንዲሁም ድርጅቶቻቸው እስካሁን መግለጫ አላወጡም፡፡