በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ወጣት ወላጅ አባት ስለ ልጃቸው አስቀድመው ለፖሊስ አሳውቀው ነበር ተባለ
ማቲው ክሩክስ የተባለ የ20 ዓመት አሜሪካዊ ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል ሲሞክር በጸጥታ ሀይሎች ተገድሏል
የአሜሪካ ሚስጢራዊ ደህንነት ሀላፊ ከስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል
በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ወጣት ወላጅ አባት ስለ ልጃቸው አስቀድመው ለፖሊስ አሳውቀው ነበር ተባለ።
የፊታችን ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ቅዳሜ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለው ወደ ህክምና መግባታቸው ይታወሳል።
ለጥቂት ከሞት የተረፉት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ ነበር ማቲው ክሩክስ በተሰኘ የ20 ዓመት ወጣት በጥይት የቆሰሉት።
የሀገሪቱ ሚስጢራዊ የደህንነት ተቋም ሰራተኞች ወዲያውኑ በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ማቲው የተገደለ ሲሆን ጉዳዩ አሁንም በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ትኩረት እንደሳበ ይገኛል።
ቢቢሲ እንደዘገበው ከሆነ የማቲው አባት ልጃቸው የተለየ ባህሪ ማሳየቱን ተከትሎ ፖሊስ ክትትል እንዲያደርግ ከክስተቱ በፊት ሪፖርት አድርገው ነበር ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ለዶናልድ ትራምፕ ድጋፍ ለማድረግ ወደ መድረኩ የመጡ ሰዎች ወጣቱ የጦር መሳሪያ ይዞ ማየታቸውን እና ሁኔታውን ወዲያውኑ ለፖሊስ አሳውቀው እንደነበር ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ሚስጢራዊ ደህንነት ጥበቃ ሀላፊ ሀላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል ተብሏል።
ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ ድጋፍ የጨመረላቸው ዶናልድ ትራምፕ በይፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በምርጫው ላይ ተቀናቃኛቸው ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ራሳቸውን ከምርጫው እንዲያገሉ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል።