ትራምፕ ሁሉንም ህገወጥ ስደተኞች ከአሜሪካ የማስወጣት እቅድ እንዳላቸው ገለጹ
ትራምፕ የወላጆች የስደተኝነት ሁኔታ ሳይጣራ ልጆች በመወለድ የሚያገኙትን የዜግነት መብትም ለማስቆም አቅደዋል

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካ የሚኖሩ ህገወጥ ስደተኞች ቁጥር እስከ ጥር 2022 ድረስ 11 ሚሊዮን እንደሆኑ ግምቱን አስቀምጧል
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉንም ህገወጥ ስደተኞች ከአሜሪካ የማስወጣት እቅድ እንዳላቸው ገለጹ።
ትራምፕ አሜሪካ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ህገወጥ ስደተኞች የማባረር እቅድ እንዳላቸው፣ ነገርግን "ህልመኛ" የሚባሉትን ስደተኞች ለመከላከል ስምምነት እንደሚያደርጉ በትናንትናው በተላለፈው የኤንቢሲ ኒውስ ቃል መጠይቃቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ትራምፕ አክለውም እንዳሉት ቢሮ በሚገቡበት የመጀመሪያ ቀን የወላጆች የስደተኝነት ሁኔታ ከግምት ሳይገባ ልጆች በመወለድ የሚያገኙትን የዜግነት መብትም ለማስቆም አቅደዋል።
ስደተኞቸን በጅምላ ለማባረር ቃል የገቡት ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫ ያሸነፉት የሪፐብሊካን እጩ ትራምፕ በጥር 20 በዓለ ሲመቻየው ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ህገወጥ ስደት ብሔራዊ አደጋ አድርገው እንደሚያውጁ እና ይህን ለማስፈጸም ከፌደራል መንግስት ሀብት ወደማሰባሰብ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካ የሚኖሩ ህገወጥ ስደተኞች ቁጥር እስከ ጥር 2022 ድረስ 11 ሚሊዮን እንደሆኑ ግምቱን አስቀምጧል። ነገርግን በአሁኑ ወቅቱ ቁጥር ከዚህ በላይ የመጨመር እድሉ ከፍተኛ ነው።
እቅዳቸው ሁሉንም ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ሰዎች ማባረር እንደሆነ በኤንቢሲ ኒውስ የተጠየቁት ትራምፕ "እኔ እንደማስበው ማድረግ አለብን" ሲሉ መልሰዋል።"ይህን ማድረግ እጅግ ከባድ ስራ ነው። ህጎች፣ መመሪያዎች አሉ።"
ትራምፕ በህጻንነታቸው ወደ አሜሪካ የመጡ "ህልመኞች" ህገወጥ ስደተኞችን ማስወጣት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ትራምፕ ከ2017-2021 በቆየው የስልጣን ዘመናቸው ለህገወጥ ስደተኞች ድጋፍ የሚያደርገውን እና ስራ የሚሰጠውን መርሃግብር ለማስቆም ሞክረው የነበረ ቢሆንም በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
የትራምፕ የዜግነት መብት የማስቆም እቅዳቸው ህጋዊ መሰናክሎች ሊያጋጥሙት እንደሚችል ተገምቷል። ይህ መብት የሚመነጨው ከአሜሪካ ህገመንግስት ማሻሻያ ሲሆን በ1898ቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔም የሚደገፍ ነው።
ትራምፕ ይህን ለማስፈጸም ሪፐብሊካኖች ህገመንግስታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ማድረግ ሊኖርባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል።
አዱስ የትራምፕ የድንበር ሹም ቶም ሆማን እና ምክትል የኃይት ሀውስ ኃላፊ ስቴፈን ሚለር የአሜሪካ ኮንግረስ የስደት ፖሊሲን ለማስፈጸም ከፍተኛ ገንዘብ መመደብ አለበት ብለዋል።
ስደትን የሚያበረታታው የአሜሪካ የስደት ምክር ቤት ከአስርት አመታት በላይ ወደ አሜሪካ የገቡ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመስ በየአመቱ 88 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ሲል ገምቷል። ሆማንም በትንሹ ይህን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።