ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እና ዩክሬን ዕብደት መቆም አለበት አሉ
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚ ዘለንስኪ ጋር በፓሪስ ተገናኝተዋል
ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እና ዩክሬን ዕብደት መቆም አለበት አሉ፡፡
በአሜሪካ ከአንድ ወር በፊት በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ በፓሪስ ታይተዋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ወደ ፓሪስ የመጡት ከሶስት ዓመት በፊት የእሳት አደጋ የደረሰበት ዝነኛው ሮተርዳም ቤተ ክርስቲያን ታድሶ ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ለመታደም ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም ዶናልድ ትራምፕ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የሶስትዮሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ዶናልድ ትራምፕ ከውይይቱ በኋላ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
“በዩክሬን ጦርነት ብዙ ሞቷል፣ ብዜ ቤተሰብ ፈርሷል እስካሁን የሆነው በቂ ነው፣ ጦርነቱ ሊቆም ይገባል” ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ጽፈዋል፡፡
“ፕሬዝዳንት ዘለንሰኪ እና ዩክሬን የሰላም ስምነምነት በቅርቡ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል፣ ይህ እብደት መቆም አለበት” ሲሉም ትራምፕ አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ ስለ ሰላም የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀው ሰላም ለዩክሬን እና ለሩሲያ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ይህ የሶትዮሽ ውይይት በተጠናቀቀ በሰዓታት ውስጥ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የጦር መሳሪያ እርዳታ የመስጠት እቅድ እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል፡፡