
ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ማዳጋስካር ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ምርጫ እያንዳንዳቸው አንድ ዕጩ አቀርበዋል
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫን ማን ያሸንፍ ይሆን?
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት የህብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ መሃማት ስልጣን ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት ቀርቶታል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ባሳለፍነው ነሀሴ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ጎረቤት ሀገር ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ማዳጋስካር እያንዳንዳቸው አንድ ዕጩ አቅርበው ጸድቆላቸዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የኬንያ ፕሬዝዳንት ለመሆን አራት ጊዜ ተወዳድረው የተሸነፉት ራይላ ኦዲንጋ በይፋ የህብረቱ ሊቀመንበር ምርጫ ተወዳዳሪ ከሆኑት መካከል አንዱ ሆነዋል፡፡
የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የራይላ ኦዲንጋ ጥያቄን በአዲስ አበባ በይፋ ያስተዋወቀ ሲሆን የምረጡ ቅስቀሳውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከኬንያ በተጨማሪም የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀሙድ አሊ የሱፍ እና የቀድሞ የማዳጋስካር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ የራይላ ኦዲንጋ ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡
እነዚህ እጩዎች የፊታችን ረቡዕ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የምረጡኝ ቅስቀሳ እንደሚያደርጉ ህብረቱ ገልጿል፡፡