
ባይደን “አሜሪካ የተከተለችው አካሄድ ለሶሪያ ህዝብና ለአካባቢው አዳዲስ እድሎች ሲከፈቱ አይተናል” ብለዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “የአሳድ መውደቅ ታሪካዊ እድል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ስልጣን ለቀው ከሀገር ከኮበለሉ በኋላ ትናንት ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ በመገናኛ ብዘሃን ቀርበው መግለጫ ሰጥተዋል።
ባይደን በመግለጫቸውም ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ መገርሰስን “ታሪካዊ እድል” በማለት የጠሩት ሲሆን፤ ሩሲያ፣ ኢራንም ሆነ ሂዝቦላ አገዛዙን ሊያድኑት አልቻሉም ብለዋል።
- ስልጣን ለቀው ከሀገር የኮበለሉት በሽር አል አሳድ ሞስኮ መግባታቸው ተነገረ
- ሩሲያ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር-አል አሳድ ስልጣን ለቀው ከሀገር መኮብለላቸውን ተከትሎ ምን አለች?
- ደማስቆን የተቆጣጠረው የሶሪያ አማጺ ቡድን በመጀመሪያ የቴሌቭዥን መግለጫው ምን አለ?
ባይደን በንግግራቸው አክለውም አሜሪካ በሶሪያ ዙሪያ በቀጣይ ስለምትወስዳቸው እርምጃቸው ያብራሩ ሲሆን፤ አሜሪካ "ከሁሉም የሶሪያ ቡድኖች" ጋር ቀርባ እንደምትነጋገር አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በንግግራቸው አክለውም ወደ ስልጣን ከመጡ ሩሲያ፣ ኢራን እና ሄዝቦላህ መዳከማቸውን ጥቅሰው፤ ይህም ለበሽር አል አሳድ መውደቅ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ የአሳድን መንግስት መገርሰስ ድል ወደራሳቸው ለመውሰድ ሲሞኩሩ ታይተዋል።
“የመረጥነው አካሄድ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የሃይል ሚዛን ቀይሮታል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
ባይደን አሜሪካ በቀጠናው የተከተለችው አካሄድ “ለሶሪያ ህዝብና ለአካባቢው አዳዲስ እድሎች ሲከፈቱ አይተናል” ብለዋል።
ለ24 ዓመታት የዘለቀው የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ማብቃቱን የሶሪያ ጦር አዛዥ ለሀገሪቱ ጦር አመራሮች ማሳወቃቸው ሮይተረስ ምንጮች ጠቅሶ መዘገቡ ይታወቃል።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ትናነት ማለዳ ላይ አውሮፕላን ተሳፍረው ስፍራው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ መኮብለላቸው ተነግሮ የነበረ ሲሆን፤ በኋላ ላይ ሞስኮ መግባታቸው የሩሲያ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
ከኢድሊብ የተነሳው ሃያት ታህሪር አል-ሻም አማጺ ቡድን ባለፉት ቀናት በአላሳድ ጦር ላይ በከፈተው ጥቃት፥ አሌፖ፣ ሃማ እና ሆምስ የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
የአማጺ ቡድኑ ግስጋሴውን በመቀጠልም ነው በትናንትናው እለት የሶሪያ ርዕሰ መዲናዋን ደማስቆ ከአላሳድ አገዛዝ ነጻ ማውጣቱን ያስታወቀው።
ይህንን ተከትሎም 53 ለሚያህሉ ዓመታት ዘልቆ የቆየው የአባትና ልጅ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱ ነው የተነገረው።