የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በመንግስት ስር ሆኖ እንደገና ሊደራጅ ነው ተባለ
ላለፉት አስርት ዓመታት ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ዩኤስኤይድ ነጻ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት ነበር
አሜሪካ በዩኤስኤይድ በኩል በዓመት ከ70 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ ላይነበረች
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በመንግስት ስር ሆኖ እንደገና ሊደራጅ ነው ተባለ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ በመላው ዓለም የረድኤት ስራዎችን የሚያግዝ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ወይም ዩኤስኤይድ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ተቋም ካቋቋመች ከ60 ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡
ይህ ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች መሰረታዊ ድጋፎችን በማድረግም ይታወቃል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ የረድኤት ድርጅት የመንገስትን ወጪ ከሚያንሩ ተቋማት መካከል አንዱ ነው በሚል ከአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታዎች ውጪ ሌሎች ወጪዎችን ለሶስት ወራት እንዳያወጣ አግደዋል፡፡
በአሜሪካ ትቅደም ፖሊሲያቸው የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ዩኤስኤይድ የግብር ከፋይ አሜሪካዊያንን ገንዘብ እያባከነ ነው የሚል አቋም አላቸው፡፡
በዩኤስኤይድ ላይ የተጣለው እገዳ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የተሰማሩ ድርጅቶችን ህልውና ከመፈታተኑ ባለፈ አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ዜጎችንም እንደጎዳ ተገልጿል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ዩኤስኤይድን አሁን ካለበት ነጻ ዓለም አቀፍ ተቋምነት ይልቅ በአሜሪካ መንግስት ስር ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ውሳኔ ለማስተላለፍ አቅደዋል፡፡
ድርጅቱ በአሜሪካ መንግስት ስር ሆኖ ከተደራጀ አሁን ያለበትን አቅም ለማስቀጠል የሚቸገር ሲሆን ከዚህ በፊት በተቋሙ ስር ሆነው አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ዜጎችንም ለከፋ ጉዳት ሊዳርግ ይችላል ተብሏል፡፡
ዩኤስኤይድ በመላው ዓለም ለሚያካሂዳቸው የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት በዓመት ከ70 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ላይ ነበር፡፡
የዶናልድ ትራምፕ አዲስ የዩኤስ እቅድ ተፈጻሚ የሚሆነው በሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ቀርቦ በአብላጫ ድምጽ ከጸደቀ ሲሆን ጉዳዩ ዋነኛ የመከራከሪያ አጀንዳ እንደሚሆንም ይጠብቃል፡፡