ትራምፕ በብሪክስ አባል ሀገራት ላይ ታሪፍ በእጥፍ ለመጨመር ዛቱ
ፕሬዝዳንቱ የብሪክስ አባል ሀገራት ዶላርን በሌላ የመገበያያ ገንዘብ እንዳይተኩ በድጋሚ አስጠንቅቀዋል
ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ 10 አባላት ያሉት ብሪክስ አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው መባሉ ይታወሳል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሪክስ አባል ሀገራት ላይ የታሪፍ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል በድጋሚ አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው እንደተገለጸ ያስተላለፉትን መልዕክት በትናንትናው እለትም "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ደግመውታል።
"የብሪክስ አባል ሀገራት የብሪክስ ገንዘብ እንደማይፈጥሩ አልያም ዶላርን የሚተካ የትኛውንም መገበያያ ገንዘብ እንደማይጠቀሙ ሊያረጋግጡልን ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን 100 ፐርሰንት ታሪፍ ይጣልባቸዋል" ነው ያሉት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው።
ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ዶላርን ላለመጠቀም የወሰኑ ሀገራት ከአሜሪካ ገበያ እንደሚሰናበቱ ማስጠንቀቃቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ የሚገቡ እቃዎች ላይ ታሪፍ መጨመርን አንዱ የፖሊሲያቸው ማስፈጸሚያ አድርገውታል።
ትራምፕ ዋይትሃውስ እንደገቡ ከካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና የሚገቡ እቃዎች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል። ውሳኔያቸውም ህገወጥ ስደትን እና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመከላከል እንደሚያግዝ አምነውበታል።
የብሪክስ አባል ሀገራትም ዶላርን የሚተካ የመገበያያ ገንዘብ እንዳይጠቀሙ ለማስጠንቀቅ የታሪፍ ጭማሪን ማስጠንቀቂያ አድርገው ደጋግመው እያነሱት ነው።
በቅርቡ ኢንዶኔዥያን 10ኛ አባሉ ያደረገው ብሪክስ 16ኛ ጉባኤውን በሩሲያ ካዛን ሲያካሂድ የራሱን የመገበያያ ገንዘብ እውን ስለሚያደርግበት ሁኔታ ምክክሮች እንደነበሩ ተገልጿል።
የቀዳሚዋ የብሪክስ መስራች ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከአለማቀፉ የገንዘብ ማስተላለፊያ ስርአት (ስዊፍት) እንድትወጣ መደረጉ ሞስኮን ክፉኛ ጎድቷታል።
ቤጂንግም ብትሆን ከዋሽንግተን ጋር የገባችበት የንግድ ጦርነት የዶላር የበላይነት ካላከተመ በምዕራባዊውያን የበላይነት የተያዘውን የአለም ስርአት መገዳደር እንደማይቻል እንድታምን አድርጓታል።
ኢትዮጵያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ እና ኢራንን ባለፈው አመት በአባልነት ያካተተው ብሪክስም ዶላርን ከገበያ ለማስወጣት ወይም ጎንለጎን አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው ተብሏል።
የባለብዙ ወገን ስብስብ - ብሪክስ
“ብሪክ” (BRIC) የሚለውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው ብሪታኒያዊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ጂም ኦኔይል ነው።
ከብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ቻይና ስያሜ የመጀመሪያ ፊደል ወስዶ “ብሪክ” የሚለውን ስያሜ ሲሰጥ በ21ኛው ክፍለዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡ ሀገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።
የአራቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፈረንጆቹ 2006 ሃምሌ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ምክክር አድርገዋል።
“ብሪክ” የሚለው ስያሜ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ሚኒስትሮቹ በመስከረም ወር 2006 ከመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በኒውዮርክ ምክክር ሲያደርጉ ነው።
የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤም በሰኔ ወር 2009 በሩሲያ አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወሳል።
“ብሪክ” ወደ “ብሪክስ” ያደገው ደቡብ አፍሪካ በ2010 በይፋ ቡድኑን ተቀላቅላ በ2011 የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ስትሳተፍ ነው።