ትራምፕ 30 ሺህ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ጓንታናሞ እንደሚልኩ ገለጹ
ፕሬዝዳንቱ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ ባህር ሃይል ጣቢያ ስደተኞችን የሚቀበል ሰፊ ማዕከል እንዲከፈት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ አስታውቀዋል
ኩባ የትራምፕን ስደተኞችን በጓንታናሞ የማሰር እቅድ "አረመኔያዊ ድርጊት" ነው በሚል አውግዛዋለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 30 ሺህ ህገወጥ ስደተኞችን ወደ ጓንታናሞ ቤይ የመላክ እቅድ እንዳላቸው ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ ባህር ሃይል ጣቢያ (ከጓንታናሞ እስርቤት የተነጠለ) ከባድ ወንጀል የፈጸሙ ህገወጥ ስደተኞች የሚታሰሩበት ማዕከል እንዲገነባ አዘዋል።
"የአሜሪካ የመከላከይ እና ሆምላንድ ሴኩሪቲ በጓንታናሞ ቤይ 30 ሺህ ስደተኞችን የሚቀበል ማዕከል እንዲያዘጋጅ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እፈርማለሁ" ብለዋል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ።
የስደተኞች ማቆያው ማዕከል በምን ያህል በጀት እንደሚሰራ እና ግንባታው መቼ እንደሚጠናቀቅ ግን የታወቀ ነገር የለም ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
በድጋሚ ወደ ዋይትሃውስ እንደገቡ ህገወጥ ስደተኞች ከአሜሪካ የማባረር ውሳኔ ያሳለፉት ትራምፕ የበርካታ ሀገራት ዜጎችን ከሀገሪቱ እያስወጡ ይገኛሉ።
በተለያዩ ወንጀሎች የሚጠረጠሩና ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች አድኖ የመያዝ ዘመቻም አስጀምረዋል።
ስለጓንታናሞ እስካሁን የምናውቀው
ጓንታናሞ ቤይ በኩባ በሚገኘው የአሜሪካ ባህር ሃይል ጣቢያ በፈረንጆቹ 2002 ነበር የተከፈተው።
ከመስከረም 11ዱ ጥቃት ማግስት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ "በሽብርተኝነት ላይ ባወጁት ጦርነት" የተከፈተው የጓንታናሞ እስርቤት የአልቃይዳ አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ታጉረውበታል።
በእስረኞች ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂ ድብደባም የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና አሜሪካውያን ጓንታናሞ እንዲዘጋ በተደጋጋሚ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አድርጓል።
የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ጆ ባይደን እስርቤቱን ለመዝጋት ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም በስልጣን ዘመናቸው ሳይፈጽሙት ቀርተዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ ባለፈው መስከረም ወር አገኘውት ያለው የመንግስት ሰነድ በጓንታናሞ የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ በባህር ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ማጎሪያ መሆኑን አመላክቷል።
ስደተኞቹ ከዋናውና በሽብር የተከሰሱ እስረኞች ከታሰሩበት እስርቤት ውጭ በሚገኝ ማቆያ ስፍራ ለአመታት ታስረው እንደሚገኙም ነው ጋዜጣው ያስነበበው።
"በስደተኞች ተወረናል" በሚል የምርጫ ቅስቀሳቸው የሚታወቁት ትራምፕ ዳግም መመረጣቸውን ተከትሎም "ወራሪ" ያሏቸውን ስደተኞች ወደ ጓንታናሞ ለመላክ አቅደዋል።
ከ11 ሚሊየን በላይ ህገወጥ ስደተኞችን ከአሜሪካ የማባረር እቅዳቸው ውስጥ ጓንታናሞን አንዱ አካል አድርገውታል።
የኩባ ተቃውሞ
የጓንታናሞ ቤይ የሚገኝባት ኩባ የትራምፕን እቅድ "አረመኔያዊ ድርጊት" ነው በሚል አውግዛዋለች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሚጉየል ዲያዝ ካነል በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁት "የአሜሪካ መንግስት በህገወጥ መንገድ በተያዘው የኩባ ግዛት፣ በጓንታናሞ ባህር ሃይል ጣቢያ ስደተኞችን ለማሰር መወሰኑ እጅግ አረመኔነት ነው" ብለዋል።
ህገወጥ ስደተኞቹ በአለማችን እስረኞችን በማሰቃየት ከሚታወቀው እስረቤት ጎን እንዲታሰሩ መታሰቡንም አጥብቀው ተቃውመውታል።