ትራምፕ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (አይሲሲ) ላይ ማዕቀብ ጣሉ
ዋይትሃውስ ሄግ የሚገኘው ፍርድቤት እስራኤልና ሃማስን በእኩል በማየት የእስር ማዘዣ ማውጣቱ "አሳፋሪ" ነው ብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/07/273-105134-ad1a9f90-e4c8-11ef-8a40-954a179da503_700x400.jpg)
አሜሪካ እና እስራኤል 120 አባላት ያሉት አይሲሲ አባል አይደሉም
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (አይሲሲ) ላይ ማዕቀብ ጣሉ።
ትራምፕ ኔዘርላንድስ ሄግ የሚገኘው ፍርድቤት "በአሜሪካ እና በአጋሯ እስራኤል ህገወጥ እና መሰረተ ቢስ ተግባር እየፈጸመ ነው" ሲሉ ከሰዋል።
በፍርድቤቱ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን፥ እርምጃው አይሲሲ በአሜሪካውያን እና አጋር ሀገራት ዜጎች ላይ የሚያደርገውን ምርመ የሚያግዙ ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።
ለፍርድቤቱ ምርመራ የሚተባበሩ አካላት የገንዘብ እና ቪዛ እቀባ እንዲደረግባቸው መታዘዙን ቢቢሲ ዘግቧል።
ትራምፕ በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ላይ ማዕቀብ የጣሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዋሽንግተን ጉብኝት እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት ነው።
ፍርድቤቱ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2024 ህዳር ወር ላይ ኔታንያሁ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል። አይሲሲ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ላይም የእስር ማዘዣ ማውጣቱ አይዘነጋም።
ዋይትሃውስ ትናንት ያሰራጨው ማስታወሻ (ሜሞ) አይሲሲ እስራኤልና ሃማስ እኩል ተመክቶ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ "አሳፋሪ" ነው ይላል።
ፍርድቤቱ በእስራኤል ራስን የመከላከል መብት ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ኢራን እና ጸረ እስራኤል የሆኑ ቡድኖችን ደግሞ ችላ ብሏል ሲልም ይወቅሳል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው አሜሪካ በአፍጋኒስታን የጦር ወንጀል መፈጸሟን የሚመረምሩ የአይሲሲ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጥለው የነበረ ሲሆን፥ በተኳቸው ባይደን ውሳኔያቸው መሻሩ ይታወሳል።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባለፈው ወር በአይሲሲ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ተስማምቶ ነበር። ይሁን እንጂ የህግ መወሰኛ ምክርቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
አሜሪካ 120 አባል ሀገራት ያሉት አይሲሲ አባል አይደለችም፤ ፍርድቤቱ በአሜሪካ ባለስልጣናት እና ዜጎች ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችንም ውድቅ ታደርጋለች።
ፍርድቤቱ የሀገራት መሪዎች ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ማምጣት ሲያቅታቸው ወይም ሳያመጡ ሲቀሩ ተጠያቂነት ለመፈጠር የሚሰራ ነው።
እስራኤልም የዚህ ፍርድቤት መመስረቻን ያልፈረመች ሲሆን፥ በጋዛው ጦርነት ምክንያት በኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ከወጣ በኋላ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ስታሰማ ቆይታለች።
አይሲሲ የሚገኝባት ኔዘርላንድስ የትራምፕን ውሳኔ "አሳዛኝ" ነው ብላለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካስፐር ቬልድካምፕ "ፍርድቤቱ ያለመከሰስ መብትን ለመዋጋት ወሳኝ ነው" ብለዋል በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።