ኦርባን በአይሲሲ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ኔታንያሁ ሀንጋሪን እንዲጎበኙ ጋበዙ
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል የሆነችው ሀንጋሪ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አስራ አሳልፋ እንደማትሰጥም ተናግረዋል
በኔታንያሁ ላይ የወጣው የእስር ማዘዣ የአውሮፓ ሀገራትን በሁለት ጎራ ከፍሏል
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት (አይሲሲ) በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ያወጣውን የእስር ማዘዣ ተቃወሙ።
አይሲሲ "የጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል" ፈጽመዋል ባላቸው ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት እና በሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሀመድ ዴይፍ ላይ በትናንትናው እለት የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።
የፍርድቤቱን ውሳኔ "የተሳሳተ፤ ድፍረት የተሞላበትና ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ የገለጹት የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር የእስራኤል አቻቸውን ቡዳፔስትን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
ኔታንያሁ ሀንጋሪ ቢገቡ የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት የእስር ማዘዣ ተፈጻሚ እንደማይሆንባቸውም ተናግረዋል።
ለስድስት ወራት የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት የሆነችው ሀንጋሪ የአይሲሲ መመስረቻን በመፈረም የፍርድቤቱ አባል መሆኗ ይታወቃል።
የፍርድቤቱ አባል የሆኑ 124 ሀገራት የእስር ማዘዣ የወጣበት ግለሰብ ግዛታቸውን እንደረገጠ በማሰር አሳልፈው ለመስጠት ስምምነት አላቸው።
ቪክቶር ኦርባን ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለምንም የደህንነት ስጋት ሀንጋሪን መጎብኘት እንደሚችሉ መግለጻቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ከፑቲን ጋር ባላቸው ቅርበትና በሚሰጡት አስተያየት ከአውሮፓ መሪዎች ጋር የሚቃረኑት ኦርባን የኔታንያሁ ወዳጅ መሆናቸው ይነገራል።
የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በኔታንያሁ ላይ ያወጣው የእስር ማዘዣ የአውሮፓ ሀገራትን በሁለት ጎራ ከፍሏል።
ኔዘርላንድስ፣ ፊንላንድ፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን እና ስፔን የፍርድቤቱን ትዕዛዝ ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆናቸውን ሲገልጹ፥ ጀርመን እና ፈረንሳይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የሀገራቱን መሬት ቢረግጡ ምን እንደሚያደርጉ በግልጽ አቋማቸውን አላንጸባረቁም።
ሌላኛዋ የአይሲሲ አባል ብሪታንያም እንዲሁ የምትሰጠውን ምላሽ እስካሁን አላሳወቀችም።
የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የሚያውል የራሱ ፖሊስ የሌለው የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት ከአባል ሀገራቱ ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመነጋገር ተጠርጣሪዎች ታስረው ተላልፈው እንዲሰጡት ያደርጋል።