እስራኤል ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ጋዛን ለአሜሪካ ታስረክባለች - ትራምፕ
ከጋዛ የሚወጡት ፍልስጤማውያን የት እንደሚሰፍሩ ያልጠቀሱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት "ምቹና ዘመናዊ ቤቶች ይገነባላቸዋል" ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/06/273-174202-gaza_167a4bc2a29e30_700x400.jpg)
የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን ከጋዛ የሚወጡበትን ሁኔታ የተመለከተ እቅድ እንዲያዘጋጅ ታዟል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በጋዛ ጉዳይ የሰነዘሩት አወዛጋቢ እቅድ ከፍተኛ ውግዘት ቢያስከትልባቸውም በዛሬው እለትም ደግመውታል።
ፍልስጤማውያንን ከጋዛ አስወጥቶ ጋዛን የመቆጣጠር እቅዳቸውን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትሩዝ ሶሻል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ጦርነቱ (የእስራኤልና ሃማስ) እንደተጠናቀቀ እስራኤል ጋዛን ለአሜሪካ አሳልፋ ትሰጣለች፤ ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲወጡ አሜሪካ ወታደሮቿን ማሰማራት አያስፈልጋትም ብለዋል።
"ፍልስጤማውያን በቀጠናው ራቅ ወዳለ፣ ደህንነቱ ወደተጠበቀና ውብ ማህበረሰብ ወደሚገኝበት ስፍራ ይዘዋወራሉ፤ አዲስና ዘመናዊ ቤቶች ይኖራቸዋል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ወደየትኛው አካባቢ እንደሚዛወሩ ግን አልጠቀሱም።
ግብጽ እና ዮርዳኖስ ቀደም ብሎ ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የቀድሞው የሪል ስቴት አልሚ ጋዛን "የመካከለኛው ምስራቅ ሬቬራ" እናደርጋታለን ሲሉም በመልሶ ግንባታው ከመላው አለም የግንባታ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከሁለት ሶስተኛ በላይ ህንጻ እና ቤቶቿ የፈራረሱባት ጋዛን መልሶ የመገንባቱ ሂደት ከ15 እስከ 21 አመት ድረስ ሊወስድ እንደሚችል የመንግስታቱ ድርጅት ማስታወቁን ሬውተስ አስታውሷል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ሚዲያቸው ለጋዛ መልሶ ግንባታ ምን ያህል ወጪ እና ጊዜ እንደሚጠይቅ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፤ አሜሪካ ግን ወጪውን በብቸኝነት እንደማትሸፍን ደግመው ተናግረዋል።
ፍልስጤማውያን የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ (በጊዜያዊነት) ከጋዛ ይወጣሉ የሚለውን አቋማቸውን ለውጠውም በቋሚነት ከቀያቸው እንደሚለቁ አመላክተዋል።
በተያያዘ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የሀገሪቱ ጦር ከጋዛ በፈቃደኝነት መውጣት የሚፈልጉ ፍልስጤማውያንን ለማስተናገድ እቅድ እንዲያዘጋጅ አዘዋል።
እቅዱ ፍልስጤማውያን በየብስ፣ በባህር እና አየር ትራንስፖርት ከጋዛ የሚወጡበትን ዝርዝር ጉዳዮችን ማካተት እንዳለበትም ተናግረዋል።
"የፕሬዝዳንት ትራምፕን ትልቅ ውሳኔ አደንቃለሁ፤ የጋዛ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ወጥተው እንዲሰደዱ ነጻነት ሊያገኙ ይገባል፤ ይህ አለማቀፍ ባህል ነው" ብለዋል።
ሚኒስትሩ "እንደ ስፔን፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ ያሉ ሀገራት እስራኤል በጋዛ ያልፈጸመችውን ፈጸመች እያሉ በሀሰት ሲከሱ ቆይተዋል፤ አሁን የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ግዛታቸው እንዲገቡ መፍቀድ ይኖርባቸዋል" ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ባሰም ናይም በበኩላቸው ካትዝ "በጋዛው ጦርነት አንዳችም ነገር ያላሳካች ሀገራቸውን ችግር ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው፤ ፍልስጤማውያን ከመሬታቸው ጋር ልዩ ትስስር ስላላቸው የትራምፕ እቅድ ተፈጻሚ አይሆንም" ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሳኡዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ግብጽና ዮርዳኖስን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ አጥብቀው አውግዘውታል።