የአይሲሲ ውሳኔ በኔታንያሁ እና እስራኤል ላይ ምን ችግር ይዞ ይመጣል?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ 124 የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል ሀገራት መጓዝ የመታሰር አደጋ ደቅኖባቸዋል
የአይሲሲ ውሳኔ በርካታ ሀገራት ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ከመሸጥ እንዲታቀቡ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተገልጿል
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
አይሲሲ ኔታንያሁ እና ጋላንት በጋዛ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነው የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው።
በኔታንያሁ እና ጋላንት ላይ የቀረበው የጦር ወንጀል ክስ "ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀም ተጠቅመዋል" የሚለውን አካቷል።
ፍርድቤቱ የጥቅምት 7ቱን የሃማስ ጥቃት አቀነባብሯል የተባለው የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ መሪ መሀመድ ዴይፍ ላይም የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ይፋ አድርጓል።
እስራኤል መሀመድ ዴይፍን በሀምሌ ወር በጋዛ ገድየዋለው ብትልም አይሲሲ ግለሰቡ መሞቱን ማረጋገጥ አልቻልኩም በሚል ነው ማዘዣውን ያወጣው።
እስራኤል የአለማቀፉን የወንጀለኞች ፍርድቤት የእስር ማዘዣ "ጸረ ሴማዊ" በሚል ስትቃወመው የፍልስጤሙ ሃማስ ውሳኔውን ደግፎታል።
የአይሲሲ ውሳኔ ለኔታንያሁ እና እስራኤል ምን ያስከትላል?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ 124 የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል ሀገራት መጓዝ የመታሰር አደጋ ደቅኖባቸዋል።
እስራኤል አጋሯ አሜሪካን ጨምሮ እንደ ቻይና፣ ሩሲያ እና ህንድ ያሉ ሀገራት የፍርድቤቱን መመስረቻ እስካሁን አልፈረሙም።
የፍርድቤቱ አባል ሀገራት የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ሰዎችን አሳልፈው ለመስጠት ስለተስማሙ ኔታንያሁ እና ጋላንት ወደ124ቱ ሀገራት መጓዝን ላይደፍሩ ይችላሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አሜሪካ ለማቅናትም በፍርድቤቱ አባል ሀገራት ማረፍ (ትራንዚት ማድረግ) አይችሉም።
የእስር ማዘዣው በውጭ ሀገራት ጉዞ ላይ ከሚፈጥረው እገዳ ባሻገር በርካታ ሀገራት መሪዋ በጦር ወንጀል የእስር ማዘዣ ለወጣባት እስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲያቆሙ ሊያደርግ ይችላል።
የኔታንያሁ አስተዳደር የእስር ማዘዣውን ቢያጣጥለውም ሀገሪቱ የጦር ወንጀል ፈጻሚ ሆና እንድትታይ በማድረግ ምስሏን እንደሚያበላሽም ነው የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት።
ኔዘርላንድስን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የፍርድቤቱን ትዕዛዝ ለማስፈጸም እየገቡት ያለው ቃልም ከ44 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ላለቁበት ጦርነት አለማቀፉ ማህበረሰብ የዘገየም ቢሆን ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።
ፍርድቤቱ የእስር ማዘዣ ሲያወጣ ሚስጢራዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ስማቸው ያልተጠቀሰ የእስራኤል ፖለቲከኞችና ወታደራዊ መሪዎችም ሊካተቱ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።
እስራኤል የአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባል አይደለችም። ፍልስጤም ግን ከ2015 ጀምሮ ፍርድቤቱን በአባልነት መቀላቀሏን ተከትሎ ነው የእስር ማዘዣው የወጣው።