ትራምፕ ለመስክ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት "አዲስ ቴስላ" መኪና እንደሚገዙ ገለጹ
በትራምፕ የተሾመው መስክ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞችን መቀነሱ አሜሪካ ውስጥ በቴስላ ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል

ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው መስክ ለሀገሪቱ "ምርጥ" ስራ እየሰራ ነው ሲሉ ተከላክለዋል
ትራምፕ ለመስክ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት "አዲስ ቴስላ" መኪና እንደሚገዙ ገለጹ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ኃላፊና አጋራቸው ለሆነው ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ድጋፋቸውን ለማሳየት አዲስ ቴስላ መኪና እንደሚገዙ ተናግረዋል። ትራምፕ ይህን ያደረጉት በቴስላ ላይ ተቃውሞ መነሳቱንና የካምፓኒው ስቶክ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ ነው።
በትራምፕ የተሾመው መስክ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞችን መቀነሱ አሜሪካ ውስጥ በቴስላ ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።ባለፈው ሳምንት ቁጥራቸው 350 ገደማ የሚሆኑ ተቃዋሚዎች በኦሪጎን ፖርትላንድ በሚገኘው የቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና መሸጫ ደጃፍ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን መጋቢት ወር መጀመሪያ ደግሞ ኒው ዮርክ በሚገኘው የቴስላ መሸጫ ቢሮ ደጃፍ ላይ በተከሰተው አመጽ የተሞላበት ተቃውሞ ዘጠኝ ሰዎች ታስረዋል።
መስክ የትራምፕ አስተዳደርን የመንግስት ውጤታማነት ዲፓርትመንትን(ዶጅ) ይመራል። ትራምፕ ትሩዝ በተባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው መስክ ለሀገሪቱ "ምርጥ" ስራ እየሰራ ነው ሲሉ ተከላክለዋል።
"ለእውነተኛው አሜሪካዊ ኢሎን መስክ ድጋፍ ለማሳየት ነገ ጠዋት አዲስ ብራንድ ያለው ቴስላ እገዛለሁ" ብለዋል ትራምፕ።
መስክ ትራምፕ ምርጫ እንዲያሸንፉ የፋይናንስ ድጋፍ ካደረጉ የአሜሪካ ቢሊነሮች ቀዳሚው ነው።
መስክም ትራምፕ ላደረጉላት ድጋፍ በኤክስ ገጹ አመስግኗቸዋል።
የመኪና ሽያጭና ትርፍ መቀነስ፣በመስክ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የተነሳው ተቃውሞና ኢንቨስተሮች በመስክ የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት ስጋት ውስጥ መግባታቸው የቴስላ ስቶክ ሽያጭ ከባለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ እንዲቀነስ ምክንያት መሆናቸው ይጠቀሳል።